አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀጣይ የሕዝብ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በትኩረት እንደሚሠራ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር እንዳሻው ጣሰው ገለጹ፡፡
የክልሉ መሥተዳድር ምክር ቤት የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
አቶ እንዳሻው በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ያለፉት ዘጠኝ ወራት ለአጠቃላይ ተግባራት መሣካት መደላድል የተፈጠረበት እና አመራሩን በአስተሳሰብ ብሎም በተግባር ለማዋሃድ የተሻለ ሥራ የተሠራበት መሆኑን አንስተዋል፡፡
መደበኛ የመንግሥት ዕቅዶችን ለማሳካትም አበረታች ሥራ መከናወኑን ጠቅሰው÷ አቅሞችንና የሕዝብ ፍላጎቶችን መለየት የተቻለበት ነው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡
በቀጣይም የሕዝብ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ፣ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ የኢንቨስትመንት፣ የግብርና እና በሌሎች መስኮችም መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት በትኩረት እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
መድረኩ በሴክተሮቹ ሪፖርቶች ላይ ተመሥርቶ ዝርዝር ውይይት በማድረግ ጥንካሬዎችንና ውስንነቶችን ያገናዘበ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተጠቁሟል፡፡