Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የተነሳው እሳት እንዳይዛመት መከላከል ተቻለ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የተነሳውን የእሳት አደጋ ለመቆጣጠር በተደረገ ርብርብ እሳቱ እንዳይዛመት መከላከል መቻሉን የፓርኩ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በፓርኩ ክልል ውስጥ አምባራስ ቀበሌ ሚያዝያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም የተነሳው እሳት በጓሳ ሳርና ውጨና በተባሉ የፓርኩ የተፈጥሮ የደን ዛፎች ላይ ጉዳት ማድረሱን ጽሕፈት ቤቱ ገልጿል፡፡

በጽሕፈት ቤቱ የአግሮ ኢኮሎጂና የዱር እንስሳት ተመራማሪ ታደሰ ይግዛው÷ በፓርኩ የዱር እንስሳት ላይ እስከ አሁን ጉዳት አለመድረሱን ጠቅሰው፤ የቃጠሎው ምክንያት በውል አለመታወቁን ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

በፓርኩ የእሳት አደጋ ተከላካይ ብርጌድ አባላት፣ በነዋሪዎችና በአጋር አካላት ተሳትፎ በተደረገው የመከላከል ሥራ ቃጠሎውን በመቆጣጠር ወደ ፓርኩ የተለያዩ አካባቢዎች እንዳይዛመት መከላከል መቻሉንም አረጋግጠዋል፡፡

ሙሉ በመሉ ለመቆጣጠርም ርብርቡ ተጠናክሮ መቀጠሉን አመላክተው÷ እሳቱ ያደረሰውን የጉዳት መጠን በዝርዝር ለማወቅም በቀጣይ በሚቋቋም ግብረ-ኃይል ጥናት ይደረጋል ብለዋል፡፡

ፓርኩ 412 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን በውስጡም÷ ዋልያ፣ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ ብርቅዬ የዱር እንስሳትና አእዋፋት ይገኙበታል።

Exit mobile version