Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አቶ ሙስጠፌ መሀመድ የሸበሌ ሪዞርት የግንባታ ሂደትን ጎበኙ

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ ክልል ርእሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ የተመራ የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ልዑክ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አካል የሆነውን የሸበሌ ሪዞርት ግንባታ ሂደት ጎብኝተዋል፡፡

ልዑኩ የችግኝ ተከላም ያካሄደ ሲሆን ÷በመርሀግብሩ ከርእሰ መስተዳድሩ በተጨማሪ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር እና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አብረሃም በላይ(ዶ/ር)፣ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር) ተገኝተዋል።

የስራ ሃላፊዎቹ የሪዞርቱን የግንባታ ሂደት እና አሁን የደረሰበት ደረጃ የጎበኙ ሲሆን÷ስለ ሂደቱንም ገለፃ ተደርጓል።

በዚህ ወቅት አቶ ሙስጠፌ መሀመድ÷ የሸበሌ ሪዞርት በክልሉ የመጀመሪያና ዘመናዊ የቱሪስት መዳራሻ መሆኑን ጠቅሰው ግንባታው ሲጠናቀቅ በአከካቢው የቱሪስት ፍሰት ከማሳደግ ባሻገር ለአከባቢው ወጣቶች የስራ እድል ይፈጥራል ብለዋል።

አክለው ፕሮጅክቱ ከፍተኛ የሀገር ሀብት የሚገነባ በመሆኑ የአካባቢው ህብረተሰብ ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ እንዲሁም ፕሮጀክቱን በባለቤትነት መንፈስ በመጠበቅ የበኩሉን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ፕሮጀክቱ በስምንት መንደሮች የተከፋፈሉ የመዝናኛ ሥፍራዎች፣ የመሰብሰቢያ አደራሾች፣ የልጆች መዝናኛ፣ 14 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገድ እና ሌሎች አገልግሎች የሚሰጡ ግንባታዎች ያካተተ መሆኑን ተመላክቷል፡፡

በሌላ በኩል በሪዞርቱ የውሃ አቅርቦት ዙሪያ በሶማሌ ክልል የዲዛይን እና ቁጥጥር ኢንተርፕራይዝ ባለሙያዎች የተሰራው ጥናት ቀርቦ ውይይት መካሄዱን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በሪዞርቱ በአጠቃላይ 1 ሚሊየን በላይ ዛፎች እንደሚተከሉ ተገልጿል።

Exit mobile version