Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ከተመድ ኤድስ (UNAIDS) ሪጅናል ዳይሬክተር ጋር መከሩ

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ከተመድ ኤድስ (UNAIDS) ሪጅናል ዳይሬክተር አን ሙዞኒ ጋር ተወያይተዋል፡፡

ዶ/ር መቅደስ ዳባ በውይይቱ ÷በኢትዮጵያ ኤድስን ለመቆጣጠር ብቻ ሳይሆን የጤና ስርአቱን በአጠቃላይ ለማሻሻል የጤና ፋይናንስ ተግዳሮት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር በትብብር በመስራት የጤና ፋይናንስ ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት እንደምትሰራም ገልጸዋል፡፡

የአፍሪካ ሀገራት ክትባትና መድሃኒቶችን በሀገራቸው ማምረት እንዲችሉ መንገድ ማመቻቸት እንደሚገባ የገለጹት ዶ/ር መቅደስ በሀገር ውስጥ የፋርማሲዩቲክል ምርቶችን ማምረት እና የጤና ፋይናንስን ማረጋገጥ የአፍሪካን የጤና ስርአት ለማጠናከር ቁልፍ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የኤችአይቪ ስርጭትን ለመከላከል፤ ስርጭቱ ከፍተኛ በሆነባቸው ክልሎች እና ወረዳዎች ትኩረት በመስጠት እንደሚሰራ፤ እንዲሁም ኤችአይቪ በደማቸው የሚገኝ ሰዎችን ማግለልን ለማስቀረት ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እንደሚሰራ ዶክተር መቅደስ ተናግረዋል፡፡

ተመድ ኤድስ የኤችአይቪን ስርጭት ለመግታት የጋጠሙ ክፍተቶችን በጥናት መለየቱን የድርጅቱ የአፍሪካ ሪጅን ዳይሬክተር አን ሙዞኒ ገልጸው በተለይም የህጻናትን በቫይረሱ መያዝ ለመከላከል ከጤና ሚኒስቴር ጋር በትብብር ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል፡፡

በኢትዮጵያ የኤችአይቪ ስርጭት በክልሎች መሃል ልዩነት እንደሚሳይ ዩኤንኤድስ እንደተገነዘበ የተናገሩት ዳይሬክተሯ ችግሩን ለመፍታት ከወረዳ ጀምሮ ትኩረት በመስጠት መሰራት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ልጃገረዶችን ትምህርት ቤት ማስገባት የኤችአይቪ ስርጭትን ለመግታት ወሳኝ መሆኑን የዩኤንኤድስ ጥናቶች እንደሚያሳዩ አን ሙዞኒ መግለፃቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version