Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የወባ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የባለድርሻ አካላት አጋርነት ወሳኝ ነው – ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የወባ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሁሉም ባለድርሻ አካላት አጋርነት ወሳኝ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ገለጹ፡፡

“ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የወባ ማስወገድ ትግበራን እናፋጥን” በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ የተከበረውን የዓለም የወባ ቀንን አስመልክቶ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በመግለጫቸውም ÷ የኢትዮጵያ መልክዓ ምድር 75 በመቶ የሚሆነው ለወባ በሽታ ስርጭት አመቺ መሆኑን ጠቅሰው ÷ 69 በመቶ የሚሆነው ህዝብም በእነዚህ አካባቢዎች እንደሚኖርና ለበሽታው ተጋላጭ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የወባ በሽታ በአብዛኛው በኢትዮጵያ የሚከሰተው የክረምት ዝናብ ተከትሎ ባለውና ከበልግ ዝናብ በኋላ ባለው ወቅት በመሆኑ አስቀድሞ በሽታውን መከላከል ካልተቻለ ሰዎችን ለህመምና ለሞት ይዳርጋል፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያ ችግርም ያስከትላል ብለዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት የወባ በሽታን በመከላከና በወባ በሽታ የሚከሰተውን ሞት በመቀነስ ረገድ ውጤት ከማስመዝገብ ባሻገር ወባን በተመረጡ ወረዳዎች ለማስወገድ ስትራቴጂ ተነድፎ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን አስታውሰዋል፡፡

ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በሽታው ባልተጠበቀ መልኩ እየጨመረ በመሄዱና በአንዳንድ ወረዳዎች በተለያዩ ምክንያቶች በወረርሽኝ መልክ በመከሰቱ የወባ ህሙማን ቁጥር ከፍ እንዲል እንዳደረገውም ተናግረዋል፡፡

ለወባ መስፋፋት መንስኤ የተለያዩ ተፈጥሯዊና ሰው-ሰራሽ ምክንያቶች እንዳሉ በመግለጽ÷ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የዝናብ መቆራረጥ በመኖሩ ምክንያት የወንዞች መቆራረጥና በየአካባቢው ያቆረ ውሃ መኖር እንዲሁም የድርቅ መከሰትን ጠቅሰዋል፡፡

ህብረተሰቡ በነፃ የሚሰጠውን በፀረ – ወባ ኬሚካል የተነከረውን የአልጋ አጎበር በትክክል አለመጠቀምና በአግባቡ አለመያዝም ለወባ መስፋፋት መንስኤ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የወባ ስርጭትን ለመከላከል በሚደረገው ርብርብ የባለድርሻ አካላት አጋርነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበው ÷ በትብብር እየሰሩ ያሉ አካላትንም አመስግነዋል፡፡

በሚኒስቴሩ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ህይወት ሰለሞን በበኩላቸው÷ ተቋማቸው የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር የወባ ምርመራና ህክምና አገልግሎትን፣ የክትትልና ግምገማ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ባለድርሻ አካላትንም በማሳተፍ የፕሮግራም ግምገማ ተደርጎ አዲስ ወባ መከላከል፣ መቆጣጠርና ማስወገድ ስትራቴጂክ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ እንደተገባም አንስተዋል፡፡

Exit mobile version