አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ሶስቱ ሀገራት ልዩነታቸውን በውይይት እንዲፈቱ ሳኡዲ አረቢያ እንደምትደግፍ በኢትዮጵያ የሳኡዲ አረቢያ አምባሳደር ሳሚ ጀሚል አብዱላሂ ገለፁ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በኢትዮጵያ የሳኡዲ አረቢያ አምባሳደር ሳሚ ጀሚል አብዱላሂን በዛሬው እለት በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በውይይቱም በሳኡዲ አረቢያ ስለሚኖሩ የኢትዮጵያ ዜጎች፣ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ እና ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
አቶ ገዱ፥ ኢትዮጵያ ከሳኡዲ አረቢያ ጋር ያላትን ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪካዊ፣ ሁሉን አቀፍ ወንድማዊ ወዳጀነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ትሰራለች ብለዋል።
ሳኡዲ አረቢያ በሀገሯ ለሚኖሩ ኢትዮያዊያን ዜጎች ስለምታደርገው ድጋፍም በማመስገን፤ “ህጋዊ በልሆነ መንገድ በድንበር በኩል ወደ ሀገሯ በሚገቡ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ያለባትን ጫና እንገነዘባለን፤ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በቅርርብና በትብብር መስራታችንን አጠናክራን እንቀጥላለንም” ብለዋል አቶ ገዱ በውይይቱ ወቅት።
ኢትዮጵያና ሳኡዲ አረቢያ ያላቸውን የዲፕሎማሲ ተሞክሮ በአቅም ግንባታና በልምድ ልውውጥ ይበልጥ ለማጠናከር እንዲቻል ሳኡዲ የስልጠና ድጋፍ እንድታደርግ አቶ ገዱ በውይይታቸው አንስተዋል።
ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የተደረጉ ውይይቶቸን በተመለከተም አቶ ገዱ ለአምባሳደሩ ገለጻ አድርገዋል።
አምባሳደር ሳሚ ጀሚል አብዱላሂን በበኩላቸው፥ ሳኡዲ አረቢያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል።
በሳኡዲ ድንበር አካባቢ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚገቡ የተለያዩ አገራት ዜጎች የሚፈጥሩትን ጫና ኢትዮጵያ በመገንዘቧ አመስግነዋል።
ሁለቱ አገሮች ከላቸው የካበተ የዲፕሎማሲ ልምድ አንጻር የአቅም ግንባታ ልውውጥ በማድረግ ላይ አተከረው እንዲሰሩ ሳአዲ ትሰራለችም ብለዋል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል እያደረገች ያለውን ጥረት በመደገፍ ሳዑዲ በትብብር ትሰራለችም ብለዋል።
ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ሶስቱ ሀገራት ያላቸውን ልዩነት በውይይት እንዲፈቱ ሳኡዲ አረቢያ እንደምትደግፍም አምባሳደሩ ገልጸዋል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

