Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ አባላት ችግኝ ተከሉ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 5 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ”ዛፍ በደጃፍ አረንጓዴ አሻራችንን እናሳርፍ” በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በመዲናዋ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ጌዲኦ ዋሻ ችግኝ ተክለዋል።

ወጣቶቹ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሃገራዊ ጥሪ መሰረት በክረምት ወራት 2 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል የያዙትን ዕቅድ ዛሬ 500 ችግኞችን በመትከል ጀምረዋል።

የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ፕሬዚዳንት ወጣት አዕምሮ አዱኛ እንደገለጸው በተያዘው ክረምት በከተማ አስተዳደሩ 7 ነጥብ 2 ሚሊየን ችግኝ የሚተከል ሲሆን ከዚህ ውስጥ 2 ሚሊየን ያህሉ በወጣቶቹ ሊግ የሚሸፈን ይሆናል።

ችግኝ መትከል ብቻም ሳይሆን የመንከባከብና የማጽደቅ ተግባር ዓመቱን ሙሉ የሚተገበሩ ይሆናል ብሏል።

የሊጉ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወጣት በቀለ ታጀበ በበኩሉ ሃገራዊውን አረንጓዴ አሻራ የማሳረፍ ጥሪ በመቀበል በተለይ ወጣቶች ሊተጉ እንደሚገባ አመልክቷል።

ዛሬ አረንጓዴ አሻራን ማሳረፍ ነገ የተሻለች ሃገር የሚረከበውን ትውልድ ለማገዝ የሚሰራ የቤት ስራ መሆኑን በመግለጽም ሁሉም የድርሻውን ሳይታክት እንዲወጣም መልዕክት አስተላልፏል።

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ሽታ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ የቀረበበትን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለማሳካት ወጣቱ በትጋት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በዘንድሮው ክረምት በሃገር አቀፍ ደረጃ የ5 ቢሊየን ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተጀምሮ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version