አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በ1974 ዓ.ም የተቋቋመው የፓቶሎጂ ሙዝየም በአዲስ መልክ እድሳት ተደርጎለት በዛሬው ዕለት ተመረቀ፡፡
የኮሌጁ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አንዱዓለም ደነቀ (ፕ/ር) በምረቃው ላይ ባደረጉት ንግግር ለበርካታ ዓመታት ለሕክምና ተማሪዎች ማስተማሪያነት ሲያገለግል የነበረው ሙዝየም÷ በቀድሞው የጤና ሚንስትር ዶክተር ከበደ ታደሰ ቤተሰቦች ድጋፍ በአዲስ መልክ ታድሶ መመረቁን አስታውቀዋል፡፡
ሙዝየሙ የጤና ባለሙያዎችን በማስተማር እና በፓቶሎጂ ዘርፍ ምርምሮችን ለማስፋፋት ያለውን ፋይዳ ጠቁመው÷ ለተማሪዎች፣ ተመራማሪዎች እና የጤና እንክብካቤ ባለሙያዎች ጠቃሚ ግብዓት እንደሚሆን ማስረዳታቸውን የኮሌጁ መረጃ አመላክቷል፡፡
የዶክተር ከበደ ባለቤት ወ/ሮ እመቤት ደጀኔ በበኩላቸው÷ የባለቤታቸውን የዶክተር ከበደ ታደሰ ራዕይ እውን ለማድረግ ቤተሰባቸው የፓቶሎጂ ሙዝየሙን በአዲስ መልክ ማዘጋጀቱን በመግለጽ ፕሮጀክቱ እንዲሳካ ላደረጉት ለጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታልና ለፓቶሎጂ ትምህርት ክፍል ምስጋና አቅርበዋል፡፡

