አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በመኖሪያ ቤቶች፣ በንጹህ መጠጥ ውኃ፣ መብራት፣ ትምህርት፣ ጤናና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶች ተጨባጭ እድገት መመዝገቡን የሶማሌ ክልል አስታወቀ፡፡
በከተማ መሬት አሥተዳደር፣ አረንጓዴ ልማት፣ ጽዳትና የከተማ ቤቶች ኪራይ ሕግ ላይ የሚመክር ሀገር አቀፍ መድረክ በጅግጅጋ ከተማ ተካሂዷል፡፡
የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ኢብራሂም ኡስማን በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ከለውጡ በኋላ የክልሉ ሕዝብ ሰላምና የፖለቲካ መረጋጋት ማግኘቱን ገልጸው÷ ይህም ለክልሉ ከተሞች ፈጣን እድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክቷል ብለዋል።
በዜጎች የኢኮኖሚና መሠረተ ልማት ዝርጋታ እንደ የመኖሪያ ቤቶች፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ፣ መብራት፣ ትምህርት፣ ጤና እንዲሁም በከተሞች ውበትና ጽዳት እና በሌሎች የማኅበራዊ አገልግሎቶች ላይ ተጨባጭ እድገትና መሻሻል ተመዝግቧል ማለታቸውን የክልሉ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል፡፡
በመድረኩ ማጠቃለያም የክልሉ ከተማ አሥተዳደሮች የሚተገብሩት መመሪያና አቅጣጫዎች ተሰጥቷል።