Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በካርቦን ግብይት ስርዓት ግንባታ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በካርቦን ግብይት ስርዓት ግንባታ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የዓየር ንብረት ለዉጥን ለመከላከል መንግስት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዲኤታ ስዩም መኮንን አስታዉቀዋል።

በአሁኑ ወቅት በዓየር ንብረት ለዉጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ እየደረሰባት የምትገኘዉ ኢትዮጵያ የተለያዩ የመከላከል ስራዎችን ብትሰራም ችግሩ ዓለማቀፍ ከመሆኑ አንጻር እንደ ጎርፍ፣ ድርቅና ሌሎች መሰል አደጋዎችን እያስተናገደች ነዉም ተብሏል።

ሚኒስትር ዲኤታዉ በኢትዮጵያ ካርቦን ንግድ ማዕቀፍ ዙሪያ በተካሄደዉ ምክክር ላይ ተገኝተዉ ፥ የዓየር ንብረት ለዉጥ ጉዳይ ዓለምን እየፈተነ ያለ እና በአሳሳቢነቱም ከፍተኛዉ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

በተለይ ጉዳቱ ለብክለቱ እምብዛም አስተዋጽኦ በሌላቸዉ ታዳጊ ሀገራት ላይ ክፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው ፥ ኢትዮጵያም የጉዳቱ ሰለባ መሆኗን አብራርተዋል።

ለዓየር ንብረት ለዉጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ መገንባት፣ የዓየር ንብረት ፖሊሲና ፕላኒንግን በአግባቡ መተግበር፣ የመላመድና ማጣጣም ስራዎችን በትኩረት መተግበር፣ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የዓየር ንብረት ለውጥ ምላሽ እቅድ፣ የረዥም ጊዜ አነስተኛ የልቀት መጠንን እዉን ከማድረግ ጄምሮ የዓየር ንብረት ለዉጥ ጉዳይ በ10 ዓመቱ ሀገራዊ እቅድ አንዱ ምሰሶ እንዲሆን ተደርጎ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

አረንጓዴ አሻራና የሌማት ትሩፋት ስራዎችም መንግስት ለዘርፉ ያለዉን ቁርጠኝነት ያሳየባቸዉ ስራዎች መሆናቸዉን ያነሱት አቶ ስዩም ፥ የታዳሽ ሃይል ልማት ሀገሪቱ ከራሷ አልፋ ጎረቤት ሀገራትን እያሳተፈቺበት ያለ ስራ ስለመሆኑም ነው የተናገሩት፡፡

የዓየር ንብረት ለዉጥ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት የካርቦን ንግድና መሰል እድል ማምጣቱን ገልጸው÷ ተጠቃሚ የመሆን ጅምሮች ቢኖሩም በሚፈለገዉ ደረጃ ለመሳተፍ ዘርፉን በህግ፣ በስርዓትና በማዕቀፍ መምራትም ያስፈልጋል ብለዋል።

ለዚህም የካርቦን ግብይት ማዕቀፍ በዓለም ባንክ ቀርቦ ዉይይት እንደተደረገበት ተጠቁሟል፡፡

ከዚህ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ሀገሪቱን ተጠቃሚ ለማድረግና የዓየር ንብረት ለዉጥን የመከላከሉን ስራ ዉጤታማ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክሩ መቀጠል እንዳለባቸዉ ያነሱት አቶ ስዩም ፥ በዚህ ረገድ የዓለም ባንክ እያደረገ ያለዉን ድጋፍም አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የዓለም ባንክ የመሰረተልማት ፕሮግራም መሪ የሆኑት ዥያወፒንግ ዋንግ በበኩላቸዉ ፥ ኢትዮጵያ ከካርቦን ሽያጭ ተጠቃሚ ለመሆኑ የምትሰራዉን ስራ በማገዝ በኩል ባንኩ ድጋፉን ያጠናክራል ብለዋል።

Exit mobile version