Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በኮቪድ19 ሳቢያ ተጋላጭ የሆኑ የከተማ ልማት ሴፍቲኔት ተጠቃሚዎችን መደገፍ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ፕሮግራም የታቀፉና በኮቪድ 19 ሳቢያ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የከተማ ልማት ሴፍቲኔት ተጠቃሚዎችን መደገፍ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ።

ስምምነቱ በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በዩኒሴፍና በዓለም የምግብ ፕሮግራም መካካል ሲሆን፥ የተገኘው የገንዘብ ድጋፍ በኮቪድ19 ምክንያት የኑሮ ጫና የደረሰባቸውን ዜጎች ለመታደግ የሚያስችል ነው ተብሏል።

በስምምነቱ መሰረት የስዊድን መንግስት በዩኒሴፍ በኩል የ116 ሚሊየን ብር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ይህም በፕሮግራሙ ለታቀፉ ቀጥተኛ ተጠቃሚዎች የሚደርስ ሲሆን የአካል ጉዳተኞችንና አረጋውያንን የሚጨምር ይሆናል ነው የተባለው።

በዚህም ለ49 ሺህ ቤተሰቦች ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ሲሆን ይህም ተጠቃሚዎቹ በመደበኛነት ከሚከፈላቸው በተደማሪነት ለስድስት ወራት የኮቪድ 19ን ጫና ለመቋቋም እንዲረዳቸው የታሰበ ነው።

በዓለም የምግብ ፕሮግራም በኩል የተገኘው ድጋፍ ደግሞ ወደ 20 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ሲሆን በ11 ከተሞች በጊዜያዊነት ለሚደረግ ቀጥተኛ ድጋፍ የሚውል ሲሆን በፕሮግራሙ ውስጥ ሆነው ነፍሰጡር የሆኑ፣ የወለዱና የሚያጠቡ እናቶችን ለመደገፍ የሚውል ሆኖ ቀደም ሲል በሚከፈላቸው ላይ በተደማሪነት ለሚደረግላቸው ድጋፍ ይውላል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሃመድ የከተማ ልማት ሴፍቲኔት ፕሮግራሙ ከ600 ሺህ በላይ ተጠቃሚዎችን ያቀፈ መሆኑን ጠቅሰው፥ የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች በአሁኑ ወቅት ኮቪድ19 ባደረሰው ጫና ምክንያት ስራቸውን በማቆማቸው ለችግር እንደተጋለጡ አመላክተዋል።

በመሆኑም ስምምነቱ በዚህ የተነሳ ለችግር እንዳይጋለጡ የማድረጉ ጥረት አካል መሆኑን ተናግረው ድጋፉን በቀጣይነት ለማድረግም በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በቀጣይም በ16 ከተሞች በድህነት ወለል ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን በመለየት መደገፍ የሚያስችል 100 ሚሊየን ብር ድጋፍ መገኘቱንና ይህንንም ወደተግባር ለመለወጥ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው ድጋፎቹ በኮቪድ 19 ምክንያት የሚያገጥሙ የኑሮና ማህበራዊ ቀውሶችን ለመታደግ የሚያግዙ መሆናቸውን ገልፀው ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸውን ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

Exit mobile version