Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ዳኛ ነኝ ጉዳይ አስፈጽማለሁ በማለት ከባለጉዳይ ጉቦ የተቀበለው የፍ/ቤት ሰራተኛ በእስራትና በገንዘብ ተቀጣ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዳኛ ነኝ ጉዳይ አስፈጽማለሁ በማለት ከባለጉዳይ 200 ሺህ ብር ጉቦ የተቀበለው የፍርድ ቤት ሰራተኛ በጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጥቷል።

የግራ ቀኝ ማስረጃን መርምሮ የቅጣት ውሳኔውን የወሰነው የኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ነው።

የኦሮሚያ ክልል ፍትህ ቢሮ አዳማ ምድብ ዐቃቤ ሕግ እንድሪስ ዑመር መሃመድ በተባለ የፍርድ ቤት ሰራተኛ ላይ የሙስና ወንጀልን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 16 ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፏል በማለት ክስ አቅርቦበት ነበር።

በዚህ በቀረበው ክስ ዝርዝር ላይ እንደተመላከተው፤ ተከሳሹ በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን ሱዲ ወረዳ ፍርድ ቤት ድጋፍ ሰጪ ሰራተኛ ሆኖ ሲሰራ የነበረና በሰው ኃይል ለማሟያ ተብሎ በጊዜያዊነት ወደ ኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የችሎት ድምጽ በመቅዳት ሙያ ላይ ተሰማርቶ በመስራት ላይ ነበር፡፡

በዚህም ለአንድ የግል ተበዳይ እራሱን ዳኛ እንደሆነ አድርጎ በመተዋወቅና በፍርድ ቤት የተያዘውን ጉዳይ እንደሚያስፈጽም በመግለጽና አሳሳች ቃላቶችን ተጠቅሞ በማሳመን ጉዳይ ማስጀመሪያ በሚል በሰኔ 20 ቀን 2015 ዓ.ም እና መዝገቡ ከተወሰነ በኋላ ደግሞ በታኅሣስ 2 ቀን 2016 ዓ.ም ለጉዳይ ማስፈጸሚያ በሚል 150 ሺህ በራሱ ስም በተከፈተ የባንክ ሂሳብ ገቢ እንዲሆንለት በማድረግ እንዲሁም ቀሪ 50 ሺህ ብሩን ደግሞ በሌላ ሰው ስም በባንክ ገቢ እንዲሆንለት ማድረጉን ጠቅሶ ዐቃቤ ሕግ በክሱ ዝርዝር አስፍሯል።

ተከሳሹም ችሎት ቀርቦ ማንነቱን ካረጋገጠ በኋላ የቀረበበት ክስ ዝርዝር ደርሶት በንባብ እንዲሰማ ከተደረገ በኋላ በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸሙን ጠቅሶ የዕምነት ክህደት ቃሉን ሰጥቷል።

ዐቃቤ ሕግ ለወንጀሉ መፈጸም የሚያስረዱ ምስክሮችንና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱም የቀረበውን ማስረጃን መርምሮ ወንጀሉ መፈጸሙን ማረጋገጡን በመግለጽ ተከሳሹ በተከሰሰበት ድንጋጌ እንዲከላከል ብይን የተሰጠ ቢሆንም ተከሳሹ ባቀረበው መከላከያ ማስረጃ በተገቢው ማስተባበል ባለመቻሉ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎበታል።

ከዚህም በኋላ ዐቃቤ ህግ ቅጣት ከብዶ እንዲጣልለት የቅጣት አስተያየት ያቀረበ ሲሆን፥ ተከሳሹም የቅጣት ማቅለያ አስተያየት አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱም የተከሳሹን የቅጣት ማቅለያ በመያዝ በእርከን 20 መሰረት በአራት ዓመት ከ5 ወር ጽኑ እስራትና በ3 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።

በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ ከባለጉዳይ የተቀበለው በባንክ ሂሳቡ የሚገኘው ገንዘብ ተወርሶ ለባለጉዳይ ተመላሽ እንዲሆን ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version