Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያና ቱርክ የንግድ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር በርክ ባራን ጋር ተወያይተዋል፡፡

አቶ ብረመስቀል÷ የግብርና ምርቶችን ወደ ቱርክ በመላክ እና የግሉን ሴክተር ግንኙነት በማጠናከር በሀገራቱ መካከል ያለውን የንግድ ሚዛን ክፍተት ማጥበብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሴክተሯን ለውጪ ባለሃብቶች ክፍት እያደረገች በመሆኑ የቱርክ ባለሃብቶች መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ቱርክ በንግድና ኢኮኖሚ፣ በቴክኖሎጂና በአቅም ግንባታ ልምዷን እንድታካፍል የጠየቁት ሚኒስትሩ÷ የቱርክ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስትመንት ለሚያደርጉት ተሳትፎ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቅሰዋል፡፡

የቱርክ አምባሳደር በርክ ባራን በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ እና ቱርክ ዘመናትን የተሻገረ የንግድና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዳላቸው አንስተዋል፡፡

በቱርክ ገበያ ቡና፣ የቆዳ ውጤቶች እና ሌሎችም የኢትዮጵያ ወጪ ንግድ ምርቶች ፍላጎት እንዳለ መግለጻቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

የሁለቱ ሀገራትን የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነት በእጅጉ ለማጠናከር ሁሉንም የንግድና ኢኮኖሚ ጉዳዮች በአንድ መድረክ አምጥቶ ለመምከር የሚያስችል የጋራ የኢኮኖሚ ኮሚሽን ለማካሄድ ከስምምነት መደረሱም ተገልጿል፡፡

Exit mobile version