አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎን ጨምሮ የቋሚ ኮሚቴ አባላት እና ባለድርሻ አካላት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን የሥራ እንቅስቃሴን ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝታቸውም ባለስልጣኑ እንደአዲስ ከተቋቋመ ወዲህ ሥራውን ለማዘመን እየተጠቀማቸው የሚገኙ ቴክኖሎጂዎችንና አጠቃላይ የባለስልጣኑን የሥራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል፡፡
በዚህም ባለስልጣኑ የሚጠቀምባቸውን የዳታ ማዕከል፣ የሕጻናት ማቆያ፣ የሃብት ክፍል፣ የሞኒተሪንግ እና ሌሎች ክፍሎችን ጎብኝተዋል፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እድሪስ ፥ ተቋማቸው የተሰጠውን ስልጣንና ኃላፊነት ለመወጣት ተቋማቸው እንደ አዲስ ከተደራጀ ወዲህ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እየተጠቀመመሆኑን ለጎብኚዎቹ አስረድተዋል፡፡
እስከ አሁንም 271 አጠቃላይ የመገናኛ ብዙሃን መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የቀጥታ ዘገባዎች ክትትል የሚደረግበት ክፍል፣ ከማኅበረሰቡ የሚመጡ ጥቆማዎች መቀበያ ክፍል፣ እንደ ፌስቡክ ቴሌግራም ቲክቶክና መሰል ማኅበራዊ ሚዲያዎች መከታየያ ክፍል ስላለው የሥራ ሁኔታም አብራርተዋል።
ከጉብኝቱ በኋላም አፈ-ጉባዔ ታገሰ የኢትዮጵያ ዲጂታል የሚዲያ አሥተዳደር ሥርዓትን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል፡፡
በምረቃው ላይ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እድሪስ እንዳሉት እነዚህ ስታርትአፖች እድል ከተሰጣቸው ለችግሮቻችን መፍትሔ ያመጣሉ ብለዋል፡፡
አንድ የሚዲያ ባለቤት ከባለስልጣኑ ጋር የሚኖረውን መረጃ በቀላሉ የሚከታተልበት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ይህ ዲጂታል ሚዲያ አሥተዳደር ሥርዓት የመገናኛ ብዙኃንን አጠቃላይ መረጃ የሚመዘግብና የሚከታተል መሆኑን ጠቁመው÷ ማኅበረሰቡም ጥቆማ የሚሰጥበትና ጥቆማው የት ደረሰ የሚለውን ጭምር የሚከታተልበት ነው ብለዋል፡፡
በሃይማኖት ኢያሱ