Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የምንዘጋጀው ለጦርነት ሳይሆን ለሀገራችን ዘላቂ ሰላምና ሉአላዊነት መከበር ነው – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የምንዘጋጀው ለጦርነት ሳይሆን ለሀገራችን ዘላቂ ሰላምና ሉአላዊነት መከበር ነው ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለፁ።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በመከላከያ የሞተር ቪሄክልስ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪን እና የመከላከያ የሜንቴናንስ መምሪያን ጎብኝተዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በዚህ ወቅት እንደገለጹት ፥ ተቋማዊ ወትሮ ዝግጁነታችንን በማረጋገጥ ተመራጭ የሰላም ሃይል ገንብተናል ብለዋል።

መከላከያ ተቋማችን ሀገርን ከውጭም ሆነ ከውስጥ የሚቃጡ ጥቃቶችን በመመከት ሰላምና ሉዓላዊነቷን እያስጠበቀ በኢንዱስትሪው ዘርፍም በመሳተፍ የራስን አቅም በራስ በመገንባት ሁለንተናዊ ለውጥ እያመጣ ይገኛልም ነው ያሉት፡፡

አሁን ላይ የተቋሙን የማድረግ አቅም ከነበረው እጥፍ በማሳደግ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም ተቋም መሆን ችለናል ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ፥ እንደተቋም በሁሉም ዘርፍ አቅምን በማሳደግ ተቋማዊ ግንባታችንን የታለመለት ግብ ላይ ማድረስ እየቻልን ነው ብለዋል።

አክለው እንዳሉትም ፥ በጦርነት ውስጥ ሆነን በሁኔታ ሳንበገር የጀመርነውን ተቋማዊ ሪፎርም በሚፈለገው ልክ ውጤታማ በሆነ መልኩ እያስኬድን እንገኛለን ማለታቸውን ከመከላከያ ሚኒስቴር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በጉብኝቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)ን ጨምሮ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ(ዶ/ር) እና የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ጀኔራል መኮንኖች ተገኝተዋል፡፡

Exit mobile version