አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ወራት በተከናወኑ ሕግ የማስከበር ተግባራት በሰሜን ሸዋ ዞን የልማት ሥራዎች እንዲከናወኑ ማድረግ መቻሉን የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ምክትል አዛዥና የሰሜን ሸዋ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ብርጋዴል ጄኔራል አበባው ሰይድ ገለጹ፡፡
በዞኑ የተሠሩ የጸጥታና የልማት ሥራዎችን የሚገመግም መድረክ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩም የኮማንዶና አየር ወለድ ዋና አዛዥና የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ጀኔራል ሹማ አብዴታ እና የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ምክትል አዛዥና የሰሜን ሸዋ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ብርጋዴል ጄኔራል አበባው ሰይድን ጨምሮ የሠራዊቱ፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች ተገኝተዋል።
ብርጋዴል ጄኔራል አበባው በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ በዞኑ የጸጥታ ኃይሉን እንደገና ማደራጀት በመቻሉ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን የተጀመሩ ሥራዎች ውጤት እንዲያመጡ አስችሏል ብለዋል፡፡
ግብርናው በአግባቡ እንዲከናወን፣ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ እና ከተሞች ሰላም እንዲሆኑ መደረጉንም አብራርተዋል፡፡
ሕዝቡ ለሠራዊቱና ለመንግሥት የጸጥታ ኃይል ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው በአጭር ጊዜ አስተማማኝ ሰላም ማስፈን እንደሚቻልም አመላክተዋል፡፡
በአላዩ ገረመው