Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሣይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ለሀገራዊ ዕድገት ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ – በለጠ ሞላ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሣይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ፈጠራ ለሀገራዊ ዕድገትና ማህበራዊ ደህንነት መጎልበት ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ ሲሉ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

“በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ያለበት ደረጃ፣ እይታ እና ተስፋዎች” በሚል መሪ ሃሳብ የውይይት መድረክ በሣይንስ ሙዚዬም እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በተለያዩ መስኮች የሚሰሩ ተመራማሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ፥ ሣይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ዲጂታላይዜሽን እና ፈጠራ ለሀገራዊ ዕድገትና ማህበራዊ ደህንነት መጎልበት ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።

የኢንዱስትሪ ምርታማነትን በማሳደግ፣ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን በመፍጠርና በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ያለውን የተወዳዳሪነት መንፈስ በማሻሻል የኢኮኖሚ እድገት እንዲኖር አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል።

የቴክኖሎጂና ፈጠራ እድት መኖር አዳዲስ ምርቶች እና አገልግሎቶች እንዲስፋፉ ምክንያት እንደሚሆኑም ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።

ይህም አዳዲስ ገበያዎችን መክፈትና የሥራ ዕድል በመፍጠር ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገትን በማምጣት ወደ ብልጽግና የሚደረገውን ጉዞ በእጅጉ ያፋጥናል ብለዋል፡፡

ባለድርሻ አካላት በመድረኩ የቀረቡ የምርምር ውጤቶችን የጋራ በማድረግ ቴክኖሎጂዎችን የማሸጋገር ሥራ እንዲሰሩ ጥሪ ማቅረባቸውንም የሚስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version