አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 6 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል በመስኖ ልማት ሊለማ ከሚችለው ከ1 ሚሊየን 75 ሺህ በላይ ሔክታር መሬት ላይ 9 በመቶ ያህሉ ብቻ መልማቱን ጥናት አመለከተ ።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ እና በክልሉ ውሀ መስኖና ኢነርጂ ቢሮ ትብብር ከ32 በላይ ባለሞያዎችንና ምሁራንን ያሳተፈ ጥናት ነበር ።
1 ሚሊየን 75 ሺህ ሔክታሩ በሚፈሱ ወንዞች የሚለማ መሬት ሲሆን ውሃ ካገኘ ሊለማ የሚችል 8 ሚሊየን ተጨማሪ ሔክታር መሬትም በክልሉ ይገኛል ተብሏል ።
ለሁለት አመታት የተካሄደው ጥናት በክልሉ ለመስኖ ልማት ሊውል የሚችል መሬትና የውሃ መጠንን በሚገባ ለይቶ ያስቀመጠ ሲሆን ያለውን የውሀ ሀብትም በሚገባ መጠቀም እንዳልተቻለም ጥናቱ አሳይቷል ።
በክልሉ ያለውን ሀብት በሚገባ አለመጠቀም ብቻም ሳይሆን ሀብቱን በሚገባ አውቆ መጠቀም ላይ ክፍተት እንዳለም ጥናቱን ያቀረቡት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ምህረት ዳናንቶ ተናግረዋል ።
በጥናቱ 47 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ለመስኖ ልማት ሊውል የሚችል የከርሰና የገፀ ምድር ውሃ በክልሉ እንደሚገኝና ይህን በአግባቡ መጠቀም ቢቻል ከክልሉ አልፎ ለሀገሪቱም ጭምር ምላሽ የሚሰጥ ነው ብለዋል ።
የባሮ አኮቦ የገናሌ ዳዋ የኦሞ ጊቤ እና የሪፍት ቫሊ አራት ታላላቅ ተፋሰሶችን አትኩሮ የተሰራ ጥናት መሆኑም ተነግሯል ።
በክልሉ ያለን የውሃ ሀብት በመጠቀም ከፍተኛ እርሻዎችን ወደ መስኖ ማስገባት እንደሚያስፈልግም የደቡብ ከልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ሀላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ የተናገሩ ሲሆን ጥናቱም ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ገልፀዋል ።
ክልሉ ይሄን ያህል ሀብት እያለው ለችግር መጋለጡ ተገቢ አይደለም ያሉት ሃላፊው ÷ አግሮ ኢንዲስቱሪዎችን ማጠናከር እና ምርት ወደ ውጭ ለመላክ መስኖ መጠቀመ ግድ ነው ብለዋል ።
የተለያዩ ሀሳቦች የተነሱበት ይህ መድረክ የተለያዩ የመንግስት ሀላፊዎች ሙሁራን የተገኙበት ሲሆን በጥናቱ የተገኙ ውጤቶች ተግባዊ እንዲሆን በቀጣይም በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ተብሏል ።
በብርሃኑ በጋሻው

