Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአማራ ክልል ሰላምን ጠብቆ ማፅናት የሁላችንም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል – መርማሪ ቦርዱ

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ጠብቆ የማፅናት ጉዳይ የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ አስገነዘበ።

ቦርዱ በባህርዳር ከተማ ተገኝቶ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ፣ ከባህርዳርና ጎንደር የኮማንድ ፖስት ዕዝ ኃላፊዎች እንዲሁም በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ተጠርጥረው በማረሚያ ቤት ከሚገኙ ተጠርጣሪዎች ጋር ተወያይቷል።

በውይይት መድረኩ ላይ የመርማሪ ቦርዱ ሰብሳቢ አዝመራ አንዴሞ እንደገለፁት፤ የየትኛውም ማህበረሰብ ጥያቄዎችን ለመመለስ በመጀመሪያ ሰላምና ፀጥታ እንዲሁም የሕግ የበላይነት መረጋገጥ አለበት።

ከሰብዓዊ አያያዝ አንጻር በማረሚያ ማዕከሉ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ መታዘባቸውን ገልፀው፤ ተጠርጣሪዎቹ ያነሷቸው ጥያቄዎች አፋጣኝ መፍትሄ እንዲያገኙ ቦርዱ በትኩረት እንደሚሰራም መናገራቸውን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በበኩላቸው፤ የክልሉን ሰላምና ጸጥታ የተሻለ ለማድረግ በተደጋጋሚ ከሕዝብ ጋር የውይይት መድረክ እየተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።

የተፈጠረው የጸጥታ ችግር እየተሻሻለ በመምጣቱ መደበኛ ልማታዊና አስተዳደራዊ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል ብለዋል።

Exit mobile version