አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ወጣቱ በመልካም ስብዕና የታነፀና አምራች ዜጋ እንዲሆን በተቀናጀ አግባብ መምራት እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።
ሚኒስቴሩ ያዘጋጀው ከሚያዚያ እስከ ሚያዚያ የጸረ-አደንዛዥ እጾችና አሉታዊ መጤ ልማዳዊ ድርጊቶችን መከላከል ላይ ያተኮረ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ የአፈፃፀም ግምገማ መድረክ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር )የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቀሰሙ ማሞ፣ ከተለያዩ ክልሎች የመጡ ሃላፊዎችና የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች ተገኝተዋል።
ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር )÷ወጣቱን ተጠቃሚ ለማድረግ የብሔራዊ የዜግነት አገልግሎት አዋጅንና መሰል የህግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት ወጣቶች ለሀገር ግንባታ የበኩላቸውን እንዲወጡ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ወጣቶች ያላቸውን ዕምቅ አቅም በመጠቀም ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማት የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ መሆናቸውን አንስተው÷ አደንዛዥ እጾችና አሉታዊ መጤ ልማዳዊ ድርጊቶች የወጣቱ ፈተና እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
የትውልድ ስብዕና ግንባታ ለጥቂት ተቋማት የሚተው ሳይሆን የሁሉንም ድርሻ የሚጠይቅ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡
ወጣቶች የነገ ተስፋ የዛሬ መሪዎች ስለሆኑ አቅሙ የተገነባና ሀገር የሚረከብ ወጣት ለመፍጠር ሁሉም ሊረባረብ ይገባል ያሉት ሚኒስትሯ÷ ወጣቶች ስብዕናቸው የታነፀ አምራች ዜጋ እንዲሆኑ በተቀናጀ አግባብ መምራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ሚኒስቴሩ ከሚያዝያ እስከ ሚያዝያ በሚል ንቅናቄ በመፍጠር በቅንጅት ሲሰራ እንደነበር መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡