አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በድሬደዋ አስተዳደር ‘በጎነት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት’ በሚል መሪ ሀሳብ የ2016 የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በይፋ ተጀመረ።
በማስጀመሪያ ስነ- ስርዓቱ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር÷ በጎ ስራ ሠብአዊነትን በማስቀድም የሚከናወንና የህሊና እረፍት የሚገኝበት የፅድቅ ስራ ነው ብለዋል።
በመሆኑም ሁሉም በንቃት ሊሳተፍበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በብልፀግና ፓርቲ የድሬዳዋ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በበኩላቸው ÷ በዘንድሮው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 14 የትኩረት መስኮች መለየታቸውን አስታውቀዋል።
በዚህም ከ260 በላይ ለሚሆኑ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች መኖሪያ ቤቶች እድሳት እንደሚደረግላቸው ተጠቁሟል።
በዚህ የክረምት በጎ ፈቃድ ስራ ላይ 86 ሺህ ወጣቶች በጎ ፈቃደኞች ይሳተፋሉ ተብሎም ይጠበቃል።
በድሬዳዋ አስተዳደር የሚከናወነውን የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በዋናነት የአስተዳደሩ ስፖርት ኮሚሽን የሚያስተባብረው ሲሆን ሌሎች የአስተዳደሩ መንግስታዊ ተቋማት ሚናቸውን ለመወጣት የሚያስችላቸውን የውል ስምምነት ተፈራርመዋል።
በምንያህል መለሰ

