አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አቡነ ሉቃስ በተከሰሱበት የቅስቀሳ ወንጀል ጥፋተኛ በተባሉበት ድንጋጌ በሥድስት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወሰነ።
የቅጣት ውሳኔውን የወሰነው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ሕገ-መንግሥታዊና በሕገ-መንግሥት ሥርዓት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮች የሚመለከተው ችሎት ነው።
የፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ በአቡነ ሉቃስ ላይ ከሦስት ወራት በፊት÷ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 247 (ሐ) እና አንቀጽ 258 (ሀ) ሥር እና የወንጀል ሕግ አንቀጽ 251 (ሐ) የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል የሚሉ ሁለት ክሶች ማቅረቡ ይታወሳል፡፡
ተከሳሹ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ-ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ አባል እና የምሥራቅ አውስትራሊያ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ፣ በጠቅላይ ቤተክኅነት የገዳማት መምሪያ የበላይ ኃላፊ ሊቀ-ጳጳስ ሆነው በማገልገል ላይ እያሉ ስለ ሰላም እና አንድነት የመስበክ ሐይማኖታዊ ግዴታቸውን በመተው ታኅሣስ 19 ቀን 2016 ዓ.ም በአሜሪካ ቴክሳስ እና አካባቢው በሚገኝ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ-ክርስቲያን ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ቤተ-ክርስቲያን ታቦት ወጥቶ በቆመበት ዐውደ-ምኅረት ላይ የአመፅ ቅስቀሳ ማድረጋቸውን የክስ ዝርዝሩ ያስረዳል፡፡
የዐቃቤ ሕግን ማስረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም የተከሰሱባቸው ክሶች በአንቀጽ 247 (ሐ) ሥር ተጠቃልሎ የጥፋተኝነት ፍርድ ማስተላለፉ ይታወቃል፡፡
በመሆኑም ዐቃቤ ሕግ ካቀረባቸው ሦስት የቅጣት ማክበጃ አስተያየቶች መካከል ፍርድ ቤቱ አንዱን የቅጣት ማክበጃ አስተያየት በመያዝ እና ተከሳሹም የቀደመ የወንጀል ሪከርድ የሌለባቸው መሆኑን መነሻ በማድረግ አንድ የቅጣት ማቅለያ ተይዞላቸው ዛሬ በዋለው ችሎት የቅጣት ውሳኔ ተሰጥቷል።
በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ በእርከን 23 ሥር በሥድስት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ በሌሉበት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
በታሪክ አዱኛ

