Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ለታማኝና ከፍተኛ ግብር ከፋዮች እውቅና ተሰጠ

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከየካቲት እስከ የካቲት “ግብር ለሃገር ክብር” በሚል የተጀመረው ሀገራዊ የግብርና ታክስ ንቅናቄ ማጠቃለያና ለታማኝና ከፍተኛ ግብር ከፋዮች የእውቅና መርሃ ግብር ተካሂዷል፡፡

በመርሃ ግብሩ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር÷ የአስተዳደሩ ገቢ በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።

በዚህም ከራስ በሚሰበሰብ ገቢ ለህዝቡ የልማት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በዚህ ዓመት 124 ነባርና አዳዲስ ፕሮጀክቶች ከ3ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተገነቡ መሆኑን ገልፀዋል።

የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ በበኩላቸው÷ ለሀገር ልማት መፋጠን የሚጠበቅባቸውን ግብር በታማኝነት የሚከፍሉ ግብር ከፋዮች አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በ2016 በጀት ዓመት 529 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው÷ ይህ ግን ካለው የመልማት ፍላጎት አንፃር ውስን በመሆኑ ገቢ በአግባቡ መሰብሰብ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ግብር ከፋዮችም የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱና በታማኝነት እንዲከፍሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

እውቅና የተሰጣቸው 75 ታማኝና ከፍተኛ ግብር ከፋዮች በፕላቲኒየም፣በወርቅና በብር ደረጃ እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።

እውቅና ለተሰጣቸው ታማኝና ከፍተኛ ግብር ከፋዮች በአስተዳደሩ በሚገኙ መንግስታዊ ተቋማት አገልግሎቶችን ቅድሚያ እንዲያገኙ የሚያስችል ልዩ መታወቂያ እንደተበረከተላቸው ታውቋል።

በተሾመ ኃይሉ

Exit mobile version