Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኮሪያ ሪፐብሊክ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮሪያ ሪፐብሊክ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በጨርቃጨርቅ፣ ብረታ ብረት እና በቡና እሴት መጨመር ዘርፍ የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ተመላከተ፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ፥ በኢትዮጵያና በኮሪያ ሪፐብሊክ መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ የሚያጠናክር ጉብኝት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በጉብኝቱ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ መዋዕለንዋያቸውን ሊያፈሱ ከሚችሉ የኮሪያ ሪፐብሊክ ባለሃብቶች ጋር ውይይት መደረጉንም ነው የገለጹት ፡፡

የኮሪያ ቴክስታይል ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን ከፍተኛ ሃላፊዎችን በማግኘት በኢትዮጵያ ያለውን ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ እንዲገነዘቡ፣ለባለሃብቶችም እንዲያሳውቁና በኢትዮጵያ ኢንቨስት ኢንዲያደርጉ ጥሪ መቅረቡን ገልጸዋል፡፡

ይህን ተከትሎ በኮሪያ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ በኩል መሰረትና ሰፊ የስራ እድል ፈጥሮ የነበረው የቴክስታይልና ጋርመንት ኢንዱስትሪ መሆኑንም ሃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡

ሆኖም ሌሎች ኢንዱስትሪዎች ቦታውን እየያዙ በመምጣታቸው ምክንያት የኮሪያ ቴክስታይልና ኢንዱስትሪ ባለሃብቶች ወደ ቬትናም፣ ማሌዥያ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ቻይና እየሄዱ መሆኑን ጠቁመው ፥ ወደኢትዮጵያም የመምጣት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል ነው የተባለው፡፡

ቀደም ሲል ወደውጪ በመላክ የሚታወቁበትን ምርት እያስገቡ እንደሆነና ምርት እያስገቡ ከሚገኙባቸው ሀገራት መካከል ደግሞ ኢትዮጵያ አንዷመሆኗንና ፤ ይህም እየጨመረ መምጣቱን መግለጻቸውን አቶ መላኩ ተናግረዋል፡፡

ይህን የበለጠ ለማጠናከርም የኮሪያ ባለሃብቶችን ወደኢትዮጵያ የመላክ ፍላጎት እንዳላቸውና ይህን ለማድረግም የፌዴሬሽኑ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ጉብኝት እንዲያደርጉ ስምምነት ላይ መደረሱን አንስተዋል፡፡

ፌዴሬሽኑ በምርምርና ጥናት፣ በሰው ሃይል ግንባታ፣ ለኢንዱስትሪዎች ገበያ በማፈላለግና ኢንዱስትሪዎችም ከምርምር ተቋማት ጋር በማስተሳሰር ትልቅ ስራ እየተሰራ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

በኢትዮጵያና ኮሪያ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከፌዴሬሽኑ ጋር ተጨማሪ ስራ እንደሚሰራ ከስምምነት መደረሱንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ቡና ከኢትዮጵያ እያስመጡ እሴት በመጨመርና በማቀነባበር ወደገበያ ያቀርቡ የነበሩ ባለሃብቶች ጋርም በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪቸውን በማቋቋም ቡናን ከምንጩ በማምረት ወደገበያ እንዲያቀርቡ ውይይት መደረጉንና ስምምነት መደረሱን ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም በኮሪያ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚዘው የብረት ፋብሪካ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ መላኩ ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የብረት ሃብት እንዳለና ሆኖም እስካሁን አለመልማቱን ተናግረዋል፡፡

በዚህም የኮሪያ የብረት ኢንዱስትሪ በኢትዮጵያ እንዲሰማራ ጥሪ መቅረቡን ገልጸው ፥ ጥሪውን ተቀብለው እንደሚመጡና ጥናት እንደሚያደርጉ ከስምምነት መደረሱንም ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጥያቄውን ለኮሪያ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት አቅርበው ፥ ጥያቄው እንደሚታሰብበትና በኢንዱስትሪ ላይ ያላቸውን ትብብር የበለጠ እንደሚያጠናክሩ መነሳቱንም ነው የገለጹት፡፡

እንደሀገር በቅርቡ በአዳማና በአዲስ አበባ የተጀመረውና ወደ ባህርዳርና ሌሎች ከተሞች እየሰፋ ያለው ስማርት ሲቲ ለከተማዋ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያበረከተ እንደሚገኝ በኮሪያው ጉብኝት ማየታቸውን አስተውቀዋል፡፡

በዚህም ከኮሪያ ሪፐብሊክ ጋር በጋራ ለመስራት ውይይት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል በጉብኝቱ ከኮሪያ ሎጅስቲክና ወደብ አገልግሎት ኢትዮጵያ ተሞክሮ መውሰዷንና በአጠቃላይ ግን እንደ ኢትዮጵያ በፈጣን እድገት ላይ ላሉ ሀገራት የኮሪያ ተሞክሮ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክት ጠቅሰዋል፡፡

በመሰረት አወቀ

Exit mobile version