አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በዘንድሮው የመኸር ወቅት 391 ሺህ ሄክታር በማልማት 17 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሠራ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
ቢሮው የ2015/16 ዓ.ም የመኸር ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና የ2016/17 ዓ.ም የመኸር ንቅናቄ መድረክ በቦንጋ ከተማ አካሂዷል፡፡
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መሥተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ማስረሻ በላቸው በመድረኩ ላይ እንዳሉት÷ ባለፉት ሁለት ዓመታት በግብርናው ዘርፍ ቅንጅታዊ ተግባራት በመከናወናቸው ተጨባጭ ለውጥ ተመዝግቧል፡፡
በዘንድሮው የመኸር ወቅትም ከ391 ሺህ ሄክታር በማልማት 17 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡
ከ880 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን በሰብል፣ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ በመሸፈን 55 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እየተሠራ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
እስከ አሁን ከ25 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን ገልጸው÷ ቀሪውን በአጭር ጊዜ ለመሰብሰብ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ምርታማነትን ለማሳደግም ያልተነኩ መሬቶችን ወደ ምርት ስርዓት ማስገባትና ቴክኖሎጂ መጠቀም እንደሚገባ መክረው÷ እስከ አሁን 168 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ጥቅም ላይ መዋሉን አንስተዋል፡፡