Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በግንባታው ዘርፍ የጥራት ችግሮችን ለመፍታት የባለሙያዎች የብቃት ምዘና ሊጀመር ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በግንባታው ዘርፍ የሚስተዋሉ የጥራት ችግሮችን ለመፍታት በቀጣይ ዓመት የባለሙያዎች የብቃት ምዘና እንደሚጀመር የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

ዘርፉ በርካታ ችግሮች ቢኖሩበትም÷ ጥራት፣ ፕሮጀክቶችን በጊዜ አለመጨረስና ሌሎች መሰል ችግሮች የሚመነጩት ከብቃት ማነስ መሆኑን በኢንስቲትዩቱ የባለሙያዎች ምዘና ሥራ ዝርጋታ ዳይሬክተር ቅድስት ማሞ ተናግረዋል፡፡

እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍም ለባለሙያዎች የብቃት ምዘና ለመስጠት ዝግጅት መጠናቀቁን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል፡፡

የብቃት ሥርዓቱም ኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪ በማድረግ፣ ተጠያቂነትን በማስፈን እና የተሻለ የፕሮጀክቶች አፈጻጸም እንዲኖር በማድግ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በተጨማሪም ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ተቋራጮችን ለመቀነስ እና ኢትዮጵያውያንም በሌሎች ሀገራት መስራት እንዲችሉ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በስምንት ዋና ዋና ክፍሎች 19 የሙያ ደረጃዎች መለየታቸውን፣ የሚያስፈልጓቸው ክኅሎቶች እና ደረጃዎች መዘጋጀታቸውን ገልጸው÷ የብቃት ምዘናው በቀጣይ ዓመት እንደሚጀመር አረጋግጠዋል፡፡

ብቃታቸው የተረጋገጠላቸው ባለሙያዎች በኢንዱስትሪው እንዲሰማሩ እንደሚደረግና የማለፊያ ነጥብ ላላመጡት ደግሞ ስልጠና በመስጠት የብቃት ምዘናውን አልፈው ወደ ኢንዱስትሪው እንዲሰማሩ ይደረጋል ብለዋል፡፡

በግንባታው ዘርፍ ከ140 ሺህ በላይ የሙያ ፈቃድ ያላቸው ባለሙያዎች መመዝገባቸውንም አስታውሰዋል፡፡

ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና ስለሚፈተኑ የብቃት ምዘናውን እንደማይወስዱም ነው ያስታወቁት፡፡

በመሳፍንት እያዩ

Exit mobile version