Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሐዋሳ ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ፕሮጀክቶች ተመረቁ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ፕሮጀክቶች ዛሬ ተመርቀዋል፡፡

ከተመረቁ ፕሮጀክቶች መካከል የፎረንሲክ ሕክምናና ሥነ-ምረዛ ማዕከል፣ የማህበረሰብ መድሐኒት ቤት፣ ስነ-አዕምሮ ሕክምና ማዕከል፣ የካንሰር ህክምና ማዕከልና የጨቅላ ሕፃናት ፅኑ ህክምና ይገኙበታል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጃ ዱጉማ ፥ መንግስት በሀገር ደረጃ ከፍተኛ የሕክምና አገልግሎቶችን ወደ ማህበረሰቡ እያቀረበ ይገኛል ብለዋል፡፡

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በሕብረተሰቡ ጤና ላይ እያደረሰ የሚገኘዉን ጉዳት ለመከላከል ችግር ፈቺ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙም ነው የገለጹት።

በዚህም ኢትዮጵያን የሜዲካል ቱርዝም ማዕከል ለማድረግ በሀገር ደረጃ የተለያዩ ስታራቴጂዎች ተቀርፀዉ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል መንግስት እየሠራ ነዉ ሲሉ ተናግረዋል።

የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አያኖ ባራሶ (ዶ/ር) ዩኒቨርስቲዉ 20 ሚሊየን ለሚሆኑ ተገልጋዮች የተለየዩ የህክምና አገልግሎቶችን እየሰጠ የሚገኝ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።

የሲዳማ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ ባራሳ በበኩላቸው እንዳሉት ፥ ማዕከሉ ሐዋሳ መከፈቱ መጉላላት የሚያስቀረና እፎይታን የሚሰጥ መሆኑን ገልፀዋል።

የካንሰር ሕክምና ማዕከሉ 100 መኝታ ክፍሎችን ያካተተ ሲሆን÷ ለህንፃ ግንባታ 400 ሚሊየን ብር ወጭ መደረጉን የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ረዳት አለሙ ጣሚሶ (ፕ/ር) ተናግረዋል።

ካንሰር ማዕከሉ በሀገር ደረጃ አራተኛ መሆኑንና ሲዳማ ክልልን ጨምሮ ለአጎራባች የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ያስመረቃቸው ፕሮጀክቶች 1 ቢሊየን ብር ወጪ የተደረገባቸው መሆኑን ከኮሌጁ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በቢቂላ ቱፋ እና በታመነ አረጋ

Exit mobile version