አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙት የልማት ስራዎች ሀገራችን ወደ ብልፅግና ለምታደርገው ጉዞ ጉልበት ናቸው ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ተናገሩ፡፡
“ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትና ክብር” በሚል መሪ ሀሳብ ህዝባዊ ውይይት በዓድዋ ድል መታሰቢያ ተካሂዷል።
የምክክር መድረኩን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ፣ የግብርናሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ በጋራ የመሩት ሲሆን÷ በውይይቱ ላይ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡
ለውይይቱ እንደ ሀገር አቀፍ የተዘጋጀውን መነሻ ፅሁፍ ያቀረቡት ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)ለኢትዮጵያ በምግብ ዋስትና ራስን መቻል የዚህ ዘመን አርበኝነት ማረጋገጫ መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ አረጋ ከበደ÷ በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙት የልማት ስራዎች ኢትዮጵያ ወደ ብልፅግና ለምታደርገው ጉዞ ጉልበት መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ለዚህ ጉዞ መሳካት ሁሉም ለሰላም፣ ለወንድማማችነትና ለአብሮነት ቅድሚያ በመስጠት የሀገራችን አንድነት እና ሉዓላዊነት በፅኑ መሰረት ላይ መገንባት አለብን ማለታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ፅ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የህብረተሰብ ክፍሎች÷ በአዲስ አበባ እየተከናወነ የሚገኘውን መሰረታዊ ለውጥ በዘላቂነት በማስቀጠል በምግብ ራስን ከመቻል አልፎ ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና ማማ የማድረስ ሀገራዊ ራዕይን እውን ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡