Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሐረርን የመጠጥ ውሀ ችግር ለማቃለል በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አቶ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ

 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)የሐረር ከተማን የዘመናት የመጠጥ ውሀ ችግር ለመቅረፍ እቅድ በማውጣት ወደ ስራ መገባቱን የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከሁለት አስርት አመታት በላይ የቆየውን የመጠጥ ውሀ ችግር ለመቅረፍ መንግስት የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን አንስተዋል።

ከ70 ኪሎ ሜትር በላይ በመጓዝ ከድሬዳዋ ሀሰሊሶ እና ድሬ ጃራ አካባቢዎች ጥልቅ የውሀ ጉድጓዶችን በመቆፈር ችግሩን ለመፍታት የተደረገውን ጥረት ለአብነት በማንሳት።

ከድሬዳዋ የሚመጣው የውሀ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ የኤሌክትሪክ ሀይል መቆራረጥ፣ የውሀ ምርት መቀነስ እና የህዝብ ቁጥር መጨመር የችግሩ ዋና መንስኤ መሆኑን አስረድተዋል።

ከድሬዳዋ ሐረር የተዘረጋው የመጠጥ ውሀ መስመር ከደንገጎ አንስቶ በማያ ከተማ ስር ለሚገኙ ሶስት ክፍለ ከተሞችም ጭምር ውሀ የሚሰጥ በመሆኑ እና በአካባቢው የነዋሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ ሐረር የሚደርሰው የውሀ መጠን ዝቅተኛ ሊሆን ችሏል ብለዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ መንግስት የአጭር ፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ወደ ተግባር መግባት መቻሉን ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ የኤረር የመጠጥ ውሀ ፕሮጀክት ላይ ማስፋፊያ በማድረግ ከአካባቢው የሚገኘውን የውሀ ምርት ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

አሁን ላይ በኤረር አካባቢ ተጨማሪ 3 ጥልቅ የውሀ ጉድጓድ ቁፋሮ ማጠናቀቅ መቻሉን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ የመስመር እና የሀይል ዝርጋታን ጉን ለጎን በማካሄድ ማጠናቀቅ መቻሉን አንስተዋል።

በቀጣይ የመስመር ፍተሻና ሙከራ በማድረግ ፕሮጀክቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ሲሉም መግለፃቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በተጨማሪም የሐረርን የውሀ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራት ከመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት እየተሰራ እንደሚገኝ ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

ከሚኒስቴሩ ጋር በመሆን በኤረር አካባቢ በቅንጅት ለሚገነባው የግድብ ስራ የጥናት እና ዲዛይን ስራ ተጠናቋል ያሉ ሲሆን ይህም የሀረርን የዘመናት የመጠጥ ውሀ ችግር በዘላቂነት እንደሚፈታ ታምኖበታል ሲሉ ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል።

Exit mobile version