አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቦትስዋና የቱሪስት መዳረሻ ወደ ሆነችው ማኡን ከተማ በረራ ጀመረ።
በማስጀመሪያው መርሐ-ግብር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስጻሚ መስፍን ጣሰው ፣የአየር መንገዱ የንግድ ዘርፍ ዋና ሃላፊ ለማ ያዴቻ በኢትዮጵያ የቦትስዋና አምባሳደር ተብሌሎ አልፈርድ ቦአንግ ተገኝተዋል።
አቶ መስፍን ጣሰው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት÷ አየር መንገዱ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ መዳረሻውን በየጊዜው እያሰፋ ይገኛል።
አየር መንገዱ አፍሪካንና አፍሪካዊያንን ለማስተሳሰር የያዘውን ውጥን ከግብ ለማድረስ በትጋት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በአየር ትራንስፖርት አፍሪካን በማስተሳሰር ለአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና መፋጠን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
አየር መንገዱ በረራ የጀመረባት ማኡን ከተማ በአፍሪካ 65ኛ መዳረሻው መሆኗን አስታውቀዋል፡፡
አየር መንገዱ ወደ ቦትስዋና ዋና ከተማ ጋቦሮኒ በረራ የሚያደርግ መሆኑን በመጥቀስ÷ የማኡን ከተማ በቦትስዋና ሁለተኛዋ መዳረሻ መሆኗን ጠቁመዋል።