Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ቀሪ የኮሪደር ስራዎቻችንን በፍጥነት ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ የምንችለውን እናደርጋለን – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቀሪ የኮሪደር ስራዎን ፍጥነትንና የፈጠራ መርህን ተከትለን አጠናቅቀን ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው፥ በተያዘላቸው የሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ፒያሳ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ዙሪያ እና የአራት ኪሎ የኮሪደር ልማት ስራዎች መጠናቀቃቸውን ጠቁመዋል፡፡

ይህን ተከትሎም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ከቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውና ከሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ጋር ገምግመናል ብለዋል።

አዲስ አበባን ከከተማው ነዋሪ ስንረከባት ልናስውባት፣ ልናለማት ቃል ገብተን ነው የጀመርነው ያሉት ከንቲባዋ፥ ለትውልድ የምትተርፍ፣ ቆሻሻ እና ስንፍና የሌለባት ከተማ ልናድርጋት ቃል ገብተን ነበር፤ እነሆ ቃላችንን ጠብቀናል ብለዋል፡፡

እንካችሁ የፀዳች አራዳን፤ እንካችሁ 24/7 የምትተጋ አራት ኪሎን፤ አሁን ለእናንተ ምቹ አድርገናታል፤ ከውበቷና ከፅዳቷ ሳትጎድል ለትውልድ አኑሯት ያሉት ከንቲባዋ፤ የኮሪደር ልማት ስራዎች ሲጀመር አብረው ለተነሱ፣ ለተባበሩ፣ ላሳመሩ ባለቤቶች፣ ለተባበሩ ባለ ሀብቶች፣ ተቋራጮች፣ በሙያቸው ለተጉ ሰራተኞችና አመራሮች ምስጋና አቅርበዋል።

ከሁሉ በላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ለነበራቸው ድጋፍና ክትትል ምስጋናዬ ትልቅ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ትናንት ምሽት ስንጎበኝ በጎዳናዎች ላይ ስራዎቹን እያደነቃችሁ ፍቅራችሁን ለገለፃችሁልን ሁሉ ከልብ የመነጨ ምስጋናችን ይድረሳችሁ በማለት ገልጸው፤ የኮሪደር ልማቱን እንዲጎበኙ ግብዣ አቅርበዋል።

ቀሪ የኮሪደር ስራዎቻችንን ፍጥነትን እና የፈጠራ መርህን ተከትለን አጠናቅቀን ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን ሲሉ ቃል በመግባት፤ ጥራትን ማስጠበቅ እና ለዜጎች ሁሉ የተመቸ ከባቢን መፍጠር ቅድሚያ የሚሰጣቸው ተግባራት መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

Exit mobile version