Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአክሱም ከተማ በ419 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነቡ መንገዶች ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአክሱም ከተማ በ419 ሚሊየን ብር ወጪ ያስገነባቸው ከ14 ኪሎ ሜትር በላይ የአስፋልት፣ የጠጠርና የድንጋይ ንጣፍ የመንገድ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል።

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የአክሱም ከተማ አስተዳደር በበጀት ዓመቱ በ950 ሚሊየን ብር ወጪ ለማከናወን ካቀዳቸው 74 ፕሮጀክቶች መካከል 46ቱ መጠናቀቃቸው ተገልጿል፡፡

የከተማዋ ከንቲባ አቶ አበበ ብርሃነ እንደገለፁት÷ እስካሁን በ419 ሚሊየን ብር በጀት ተገንብተው ከተጠናቀቁት ፕሮጀክቶች መካከል የአስፋልትና የጠጠር መንገዶች፣ የጎርፍ መውረጃ ቦይ እና የድንጋይ ንጣፍ መንገድ ይገኙበታል።

ከዚህ ውስጥም በ311 ሚሊየን ብር በጀት የተገነባው 1 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ግንባታው ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በ108 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባ የ13 ኪሎ ሚትር የውስጥ ለውስጥ የድንጋይ ንጣፍና የጠጠር መንገድ ግንባታ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት መብቃቱን ነው የገለጹት፡፡

በጠጠር መንገድ ግንባታው ከ1 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ከንቲባው ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

Exit mobile version