አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ5 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታር በላይ በዘር ለመሸፈን ታቅዶ እየተከናወነ ባለው ሥራ እስከ አሁን 4 ሚሊየን ሄክታር የሚጠጋ መሬት መታረሱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
በክልሉ በ2016/17 የመኸር ምርት ዘመን ከ169 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ ነው ያለው ቢሮው÷ ዕቅዱን ለማሳካት የክረምት ስራዎች የንቅናቄ መድረክ ከክልል ጀምሮ እስከ መንደር ድረስ መሰጠቱን አስታውቋል፡፡
በክልሉ ከ5 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታር በላይ በዘር ለመሸፈን ታቅዶ እስከ አሁን 4 ሚሊየን ሄክታር የሚጠጋ መሬት ታርሶ ከ600 ሺህ ሄክታር የሚልቀው ደግሞ በዘር መሸፈኑን አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል እስከ አሁን 4 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ዩኒየኖች መጓጓዙን እና ከዚህ ውስጥ ከ4 ሚሊየን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች መሠራጨቱን የቢሮው መረጃ አመላክቷል፡፡