አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2017 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት 971 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ሆኖ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል።
ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ ያቀረቡትን የፌዴራል መንግሥት የ2017 በጀት ዓመት ረቂቅ የበጀት መግለጫ አዳምጧል፡፡
የ2017 በጀት ዓመት የፌደራል መንግሥት ረቂቅ በጀት እስከ አሁን ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉትንና በቀጣይ ለመተግበር የታቀዱትን እንዲሁም የኢኮኖሚ እድገቱን ለማስቀጠልና የተዛባውን የማክሮ ኢኮኖሚ ለማስተካከል በሚያግዝ መልኩ መዘጋጀቱን ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡
የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠርም የገንዘብ ፖሊሲውን ዘመናዊ ማድረግ የሚያስችሉ ማሻሻያዎች ተግባራዊ እንደሚደረጉ አመላክተዋል፡፡
የውጭ መዳረሻ ገበያዎችን በማስፋት የሚላኩ ምርቶችን ዓይነትና መጠን እንዲሁም ጥራት ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
የውጭ እዳ ስጋት መቀነስ የፊሲካል ቁመናችንን ለማሻሻል አስፈላጊ ነው ያሉት ሚኒስትሩ÷ ይህም ልማትን ለማፋጠን የሚቀረጹ አዋጪ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የፋይናንሲንግ አቅም ለማግኘት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
ከአበዳሪዎች ጋር የተጀመሩ የእዳ ሽግሽግና የእዳ ማቃለያ ድርድሮችን ውጤታማ በማድረግ ይህንን ማሳካት እንደሚገባም ነው በአጽንኦት የገለጹት፡፡
ረቂቅ በጀቱ ቅድሚያ ትኩረት የሚደረግባቸው የገቢና ወጪ የፊሲካል ፖሊሲ አቅጣጫዎችን፣ ወቅታዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታንና የኢኮኖሚ ማሻሻያውን የትኩረት አቅጣጫ ባገናዘበ መልኩ መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል፡፡
የፌደራል መንግስት የ2017 በጀት አመት ጠቅላላ ወጪ በጀት 971 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር መሆኑን ጠቅሰው÷ ይህም ለ2016 በጀት አመት ከጸደቀው የወጪ በጀት አንጻር የ21 ነጥብ 1 በመቶ እድገት እንዳለው አስታውሰዋል፡፡
ከዚህ የወጪ በጀት ውስጥ 451 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ለመደበኛ፣ 283 ነጥብ 2 ለካፒታል እንዲሁም 236 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ለብሔራዊ ክልሎች መንግስታት የተመደበ በጀት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የተመደበላቸውን በጀት ለታለመለት አላማ በቁጠባና በላቀ ውጤታማነት ጥቅም ላይ ማዋል እንዳለባቸውም ነው ያሳሰቡት፡፡
የምክር ቤት አባላትም በተለያዩ ክልሎች የሚታዩ ሰላምን የሚያደፈርሱ ክስተቶች ወደ ሰላማዊ ሁኔታ መምጣት እንዳለባቸው ጠቁመው÷ የውኃ፣ መብራት፣ መንገድ መሰረተ-ልማት ላይ የገንዘብ ሚኒስቴር ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡
በየሻምበል ምኅረት