Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የግብርናውን ዘርፍ ስኬት ለማስቀጠል ያለሙ ማሻሻያዎች ተደርገዋል- ሚኒስቴሩ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በግብርናው ዘርፍ የመጣውን ተጨባጭ ለውጥ ለማስቀጠል በፋይናንስ አቅርቦት ላይ ማሻሻያ መደረጉን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንት ተግዳሮቶችና ቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ የፌዴራል እና የክልል የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት የተገኙበት መድረክ ተካሂዷል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ በግብርናው ዘርፍ የመጡ ተጨባጭ ለውጦችን በመግለጽ የመጣውን ለውጥ ለማስቀጠል የፋይናንስ አቅርቦት ላይ ማሻሻያዎች ተደርገዋል ብለዋል፡፡

በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ማሳሰባቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡

የግብርና ኢንቨስትመንትና ግብዓት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ሶፍያ ካሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የግብርናውን ዘርፍ የኢኮኖሚ ድርሻ ከፍ ለማድረግ የግል ባለሃብቱን ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

መንግሥት የግብርና ኢንቨስትመንት ላይ የፖሊሲ ማሻሻያዎች፣ የመሬት፣ የመሰረተ-ልማት እና የፋይናንስ አቅርቦት ላይ በትኩረት እየሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክም የግብርናው ዘርፍ ለኢኮኖሚ ዕድገት ያለውን ሚና ተረድቶ የወለድ ምጣኔውን ከ11 ነጥብ 5 ወደ 7 በመቶ ዝቅ በማድረግ ባለሃብቱ በዘርፉ እንዲሳተፍ እያበረታታ መሆኑን የባንኩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

Exit mobile version