አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የገንዘብ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ቆላማ ቦታዎች ድህነትን እና ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚያስችል ጥናት ላይ የቪድዮ ኮንፈረስ አካሄደ።
በዚህ የገንዘብ ሚኒስቴር በበላይነት በሚመራውና በአለም ባንክ እና በእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ተቋም ጋር በመተባበር በሚያካሂደው ጥናት ላይ የሚኒስትሮች፣ የክልል መንግስታት ተወካዮች እና የልማት አጋሮች ተሳትፈዋል፡፡
ጥናቱ በኢትዮጵያ ቆላማ ቦታዎች ላይ ድህነት እና ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚረዳ በማስረጃ ላይ የተመሠረተ የፖሊሲ ምክረ ሀሳብ ከማቅረቡም ባለፈ ችግሮቹን በዘላቂነት ለመቋቋም አመላካች መንገዶችን በጥናቱ መቀመጡ ተነስቷል።
ከዚያ ባለፈ ጥናቱ በሀገሪቱ በቆላማ ቦታዎች ላለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በዋናነት የድህነት መጠን መቀነሱን ቢያመላክትም አሁንም በአካባቢው ያለው የገቢ መጠን ዝቅተኛ መሆኑ ተገልጿል።
ስለሆነም በቆላማ ቦታዎች ድህነትን እና ተጋላጭነትን በዘላቂነት ለመቀነስ ጥናቱ በሰብዓዊ ካፒታል ውስጥ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡
ከዚያም ባለፈ የአስተዳደር ስርዓቱን እና የደህንነት መረብ ፕሮግራሞችን በተሻለ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓቶችን ማጎልበት እና ድንበር ተሻጋሪ የእንስሳት ገበያ ጋር የተዛመዱ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን መፍታት እንደሚገባም አመላክቷል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በወቅቱ ባስተላለፉት መልእክት÷ እነዚህ ቆላማ የሀገሪቱ አካባቢዎች በአርብቶ አደሮች 60 በመቶ የሚሸፍኑ ሲሆን፥ 12 በመቶ ለሚሆነው የሀገሪቱ ህዝብ ደግሞ መኖሪያ ነው ብለዋል።
ስለሆነም ቆላማ ቦታዎች ያላቸውን አቅም ሙሉ በሙሉ በመጠቀም ፣ የሰው ሀብት ልማትን እና የአስተዳደራዊ የአቅም ክፍተቶችን መፍታት እና በመሠረተ ልማት ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል ፡፡
በጥናቱ የተገኙ ግኝቶች እና የውሳኔ ሃሳቦች ላይ በመመርኮዝ የጥናቱን የውሳኔ ሃሳብ በማፅደቅ እና የአርብቶ አደር አካባቢ ልማት ስትራቴጂ በመቅረጽ ጥናቱ በብሔራዊ የ10 ዓመት ዕቅዱ ውስጥ እንዲካተት ከስምምነት ላይ ተደርሷል ፡፡
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

