አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጤናው ዘርፍ የመካከለኛ ዘመን የልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅድ የሀገር ውስጥ ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ የገበያ ድርሻን ወደ 47 በመቶ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የሀገር ውስጥ የሕክምና ግብዓት የምርትና ኢኖቬሽን ኤግዚቢሽንን በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ መርቀው ከፍተዋል።
ኤግዚቢሽኑ በጤና ሚኒስቴርና የሀገር ውስጥ የሕክምና ግብዓት የምርትና ኢኖቬሽን ዘርፍ ማኅበራት ትብብር “ጤናችን በምርታችን” በሚል መሪ ኃሳብ የተዘጋጀ ሲሆን÷ ከሰኔ 15 እስከ 20 ቀን 2016 ዓ.ም ለጉብኝት ክፍት ሆኖ ይቆያል።
በዚሁ ጊዜ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ÷መንግሥት የጤናውን ዘርፍ በማሻሻል የፈውስ ሕክምናን ማዕከል ያደረገ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ላይ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።
በእናቶችና ህፃናት፤ በዜጎች ጤና ላይ ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታ መከላከል መስክ ተጨባጭ ለውጥ የተመዘገበ ቢሆንም በፋርማሲቲካል ኢንዱስትሪ መስክ ግን ተጨማሪ ሥራ እንደሚጠይቅ ገልፀዋል።
የሕክምና ግብዓት አቅርቦት ሥርዓቱን በጤናና የመድኃኒት ፖሊሲ፣ ዕቅድና መምሪያ በማዘጋጀት ኢትዮጵያ በሕክምና ግብዓት ራሷን የምትችልበት የትኩረት አቅጣጫ ተነድፎ እየተሰራ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በአሥር ዓመቱ ብሔራዊ የመድኃኒት አምራች ኢንዱስትሪ ስትራቴጂክ ዕቅድ በጤናው ዘርፍ የመካከለኛ ዘመን የልማት ኢንቨስትመንት ዕቅድ የሀገር ውስጥ የፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ የገበያ ድርሻን 47 በመቶ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያን የሀገር በቀል መድኃኒት የመገልገል ዕውቀትና ባህል ከዘመናዊ የሕክምና አሠራር ጋር በማጣመር ወደ ውጤት ለመቀየር በጥናትና ምርምር የተመሠረተ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

