አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ እንደሚገኙ የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ አስታውቋ።
ቢሮው የ100 ቀናት እቅዱን ለማሳካት ያደረገውን የመስክ ድጋፍ፣ ክትትልና ቀጣይ አቅጣጫ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በባህር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው።
በም/ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአማራ ክልል የአስተዳደር ዘርፍ አስተባባሪና የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው÷ የክልሉን ሰላም ለማስከበር የፀጥታ ሃይሉን አደረጃጀት እንዲያጠናክር የአመራር ቡድን ተልዕኮ ወስዶ ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።
በዚህም የክልሉ ሰላም መሻሻል እያመጣ መሆኑን ጠቅሰው÷በክልሉ ሰላምን ዘላቂ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት አሁንም በትኩረት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የዛሬው መድረክ ቡድኑ በሚያቀርበው የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ተመስርቶ በየደረጃው ያለው የፀጥታ መዋቅር ያለበትን ቁመና በመገምገም መልካም ተሞክሮን ለማስፋት ቀጣይ አቅጣጫ የሚቀመጥበት መሆኑን አስረድተዋል።
እንዲሁም ችግሮችን በመፍታት የህዝቡን ሰላምና ደህንነት የማረጋገጡ ተግባራትን ለማመቻቸት እንደሚያስችል ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ለሰላምና መልካም አስተዳደር ሥራዎች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ያለመ መድረክ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በመድረኩ የሚገኙ ግብዓቶችን በመጨመር ለቀጣይ ሥራዎች ዝግጅት እንደሚደረግ አብራርተዋል።
በመድረኩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የጸጥታ ዘርፍ አመራር አባላት በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ተመላክቷል።

