Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በክልሉ በምሽት እየተከናወነ የሚገኘው የልማት ስራ የክልሉን የስራ ባህል የቀየረ ነው-አቶ ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀረሪ ክልል በምሽት እየተከናወኑ የሚገኘው የልማት ስራ የክልሉን የስራ ባህል የቀየረ ነው ሲሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለፁ።

የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ከካቢኔያቸው ጋር በመሆን ለ26ኛው የሀረር ቀን በከተማው በምሽት እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።

አቶ አርዲን በድሪ በዚህ ወቅት÷በከተማው በምሽት እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች የክልሉን የስራ ባህል የቀየሩ እና የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የልማት ስራዎችን በምሽት ማስቀጠል መቻሉ በ2016 በጀት ዓመት የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በፍጥነት በማጠናቀቅ በቀጣዩ በጀት ዓመት ለማከናወን በዕቅድ የተያዙ የልማት ስራዎችን በፍጥነት ለማስጀመር የሚረዳ መሆኑንም ገልፀዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይም የልማት ስራዎችን በተያዘላቸው ግዜ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ ስራዎችን በቀን ብቻ ሳይሆን በምሽት የማከናወኑ የስራ ባህል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚቀጥል መግለፃቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በከተማው ዋና ዋና መንገዶች የተተከሉ የመንገድ ዳር መብራቶች ፣ ከተማዋን ለማስዋብ እየተከናወኑ የሚገኙ የፅዳት እና አረንጓዴ ልማት ስራዎችን ጨምሮ ለሀረር ቀን ማክበሪያ ስፍራዎች ዝግጅት የመስክ ምልከታ ከተደረገባቸው የልማት ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው።

Exit mobile version