Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ዶናልድ ትራምፕ በፖሊስ ኃይል ላይ አዳዲስ ማሻሻያዎች እንዲካሄዱ የሚያደርግ ፕሬዚዳንታዊ ውሳኔ ፈረሙ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 10 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በፖሊስ ኃይል አባላት ላይ አዳዲስ ማሻሻያዎች እንዲካሄድ የሚያደርግ ፕሬዚዳንታዊ ውሳኔ ፈረሙ።

የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ ለፖሊስ የሚመደብ በጀትን በማሳደግ፥ አሰራሩን ለማዘመን ያለመ ስለመሆኑ ነው የተነገረው።

ከዚህ ባለፈም ተጠርጣሪዎች ላይ አላግባብ ድርጊት የሚፈጽሙና ሃይል የሚጠቀሙ የፖሊስ አባላትን መከታተልና መቆጣጠር የሚያስችል አሰራር መዘርጋትንም ያካተተ ነው።

ዶናልድ ትራምፕ ፖሊስ የሚያገኘው በጀት እንዲቋረጥ የቀረበላቸውን ሃሳብ ግን ውድቅ አድርገውታል።

የዛሬው ፕሬዚዳንታዊ ውሳኔያቸው ከሰሞኑ በጥቁር አሜሪካዊ ጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ምክንያት መጥፎ ድባብ ውስጥ የገባውን የዋሽንግተንን ፖለቲካ ለመታደግ ያለመ ነው ተብሏል።

በውሳኔው መሰረትም ፖሊሶች ተጠርጣሪዎች ላይ ሃይል መጠቀምና አንገት ማነቅ አይፈቅድላቸውም።

አዲሱ ማሻሻያ ሕግ አስፈጸሚ አካላት ላይ ተግባራዊ የሚደረግና የሚያስገድድ ሕግ ነውም ነው የተባለው።

አንዳንድ ፖለቲከኞች ግን የትራምፕን አዲስ ውሳኔ “ጊዜያዊ፣ ብዙሃኑ የሚፈልጉትን ለውጥ የማያመጣና በፖሊስ ክፍሉ ላይ በአግባቡ ተጠያቂነት የማያሰፍን” ሲሉ ነቅፈውታል።

ከዚህ ባለፈም ፖሊስ በጥቁር አሜሪካውያን ላይ የሚያደርሰውን አሰቃቂ ጉዳት እና የሚፈጽመውን ዘረኝነት ለመከላከልና ለመቅረፍ አቅም የሚያንሰውም ብለውታል።

በአሜሪካ ፖሊሶች በተለይም ጥቁር አሜሪካውያን ላይ የበዛ ሃይል ይጠቀማሉ።

በዚህ ሳቢያም በርካቶች ለህልፈት የተዳረጉ ሲሆን፥ ከሶስት ሳምንታት በፊት በሚኒያፖሊስ ከተማ በፖሊስ በአሰቃቂ ሁኔታ ለህልፈት የተዳረገው ጆርጅ ፍሎይድም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

የ46 አመቱን ጎልማሳ ህልፈት ተከትሎም በተለይም በአሜሪካ አመጽ የተቀላቀለባቸው የተቃውሞ ሰልፎች ተካሄደዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ህግ አውጭዎች ፖሊሶች ያልተመጣጠነ ሃይል እንዳይጠቀሙ የሚያደርጉ መመሪያዎች ሲያዘጋጁም ቆይተዋል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Exit mobile version