Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በኦስሎ ትሮፒካል ደን ፎረም ላይ አድናቆት ተቸረው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ በኖርዌይ እየተካሄደ በሚገኘው የኦስሎ ትሮፒካል ደን ፎረም ላይ እየተሳተፈ ነው፡፡

ልዑኩ ኢትዮጵያ የቀጣናው ሀገራት ጭምር የትሩፋቱ ተካፋይ የሆኑበትን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የባለፉት ዓመታትን ውጤት፣ የደን ጭፍጨፋ መቀነስና የደን ሽፋን እድገት በጉበዔው አንስቷል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ለአረንጓዴ አሻራና ለተራቆቱ መሬቶች ማገገሚያ በሚኒስትሮች ም/ቤት ስላጸደቀው የልዩ ፈንድ አዋጅና ከዚህ ጋር ተያይዞ የመንግስትን የላቀ ቁርጠኝነትም ልዑኩ በጉበዔው አብራርቷል፡፡

ከዚህ ባለፈም የበጋ ስንዴና የሌማት ትሩፋት ስራዎች የምግብ ፍጆታና ሥርዓተ-ምግብ ከማሟላት ባሻገር ለደን ጭፍጨፋ መቀንስና ለደን ሸፋን እድገት ያላቸውን አስተዋጽኦና ኢትዮጵያ ጤናው የተጠበቀ ማህበረሰብ ለመገንባት ምርት ከማምረት እስከ አጠቃቀም ሊኖር የሚገባ ስርዓት እንዲገነባ እየሰራች መሆኑ በጉባኤው ተጠቅሷል፡፡

ኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግና የተፈጥሮ ሃብት በዘላቂነት እንዲጠበቅና ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ የሰራቻቸው ጉልህ ሥራዎች በመልካም ተሞከሮነት በጉባዔው ጭምር ቀርበው አድናቆት እንደተቸራቸው ተጠቁሟል፡፡

ልዑኩ ከጉባዔው ጎን ለጎን ከኖርዌይ የአየር ንብረት እና የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር እንዲሁም ከኖርዌይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መክሯል፡፡

በተጨማሪም ከኖርዌይ ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተርና ከኖርዌይ ዓለም አቀፍ አየር ንብረትና ደን ኢኒሼቲቭ ም/ዋና ዳይሬክተር ጋር ውጤታማ ውይይት አድርጓል፡፡

በሁለትዮሽ ውይይቱ የኖርዌይ ባለስልጣናት ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም እያከናወነች ያለውን ተግባር፣ የሙቀት አማቂ ጋዝ ለመቀነስና የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ብሎም የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የሚኖረውን ትልቅ ፋይዳ ማድነቃቸው ተገልጿል፡፡

የሁለቱ ሀገራት ትብብር የበለጠ እንዲጠናከር የድርሻቸውን እንደሚወጡ ማረጋገጣቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version