Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የመጀመሪያው የውሃ ሙሌትን ለማከናወን መንግስት የያዘውን አቋም አጠናክሮ ሊቀጥልበት እንደሚገባ ምሁራን ገለፁ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የመጀመሪያው የውሃ ሙሌትን ለማከናወን መንግስት የያዘውን አቋም አጠናክሮ ሊቀጥልበት እንደሚገባ ምሁራን ገለፁ።

ከፋና ብሮድካስቱንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት ምሁራኑ ፤ ግብጽ ባለፉት 5 ቀናት በተደረገው የ3ቱ ሀገራት ድርድር ያንጸባረቀችው ግትርነት የውሃ ሙሌቱን ከዚህ ክረምት ለማደናቀፍ ያሴረ ነው ብለዋል።

የወሎ ዩኒቨርስቲ የህግ መምህሩ አቶ ደጀኔ የማነ እንዳሉት ካይሮ ከቀኝ ግዛት ውሎች ትርክቶቿ የወጣች መስላ የሶሰትዮሽ ድርድሩ ላይ ብትታይም ፤ ሰቶ ለመቀበል ግን ዝግጁ አለመሆኗን በተደጋጋሚ አሳይታለች ነው ያሉት።

መንግስት የውሃ ሙሌቱን በታቀደበት ጊዜ ለማከናወን እያደረገ ያለው ጥረትም ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን ተናግረዋል ።

በአባይ ላይ መጽሃፍ ያሳተመው የዘርፉ ምሁር ኢንጂነር ብሩክ ወልደየስ በተደጋጋሚ በድርድሮች ላይ በግብጽ በኩል የታየው ጠባይ አሁን ላይ የተለመደ ይሁን እንጂ ፤ መንግስት የካይሮ ሁናቴ ውሃ ከመሙላት ለማደናቀፍ የሚደረግ ማደናገሪያ ጊዜ መግዣ መሆኑን ሊገነዘብ እንደሚገባ ይናገራሉ ።

የመንግስትን ቆራጥ አቋም ያደነቁት ምሁራኑ የአባይ 86 በመቶ ድርሻ ያላት ሀገር የዘመናት የትውልድ ጥያቄን መልስ መስጠት በቀጣዩ ወር ውሃ በመሙላት መጀመር እንሚኖርባት ገልፀዋል።

ህዝቡም መንግስት የውሃ ሙሌት ለማድረግ እያደረገ ያለውን ጥረት በአንድነት በመቆም ሊያግዝ እንደሚገባም አሳስበዋል ።

በሀይለየሱስ መኮንን

Exit mobile version