Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ጠንካራ ስነ ልቦና ችግሮችን መሻገሪያ ድልድይ ነው- ወጣት በለጠ ቡቱና

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጠንካራ ስነ ልቦና አለመቻልን ወደ መቻል የቀየረው በለጠ ቡቱና የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል አንዱ ነው፡፡

በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ያለፉትን አምስት ዓመታት በማታው የትምህርት መርሐ ግብር በማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ትምህርቱን ሲከታተል የቆየው ተማሪ በለጠ ቡቱና ጠንካራ ስነ ልቦና ካለ የማይታለፍ መንገድ የለም ብሏል።

ወጣት በለጠ ወላጅ እናትን በልጅነት ማጣትን ጨምሮ ህይወቱን በርካታ ፈተናዎችን ተጋፍጧል።

የአካል ጉዳት ያለበት ወጣት በለጠ አጋዥ አባትም የሌለው በመሆኑ የመኖር ተስፋውን ሊያደበዝዝ ቢችልም ለችግርና ለፈተና እጅ ባለመስጠት ጉዞውን ማስቀጠል ችሏል።

የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ሲያመጣ በሲዳማ ክልል አርቤጎና ወረዳ የ20 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ ከተደረገለት በኋላ ወደ ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ አቅንቷል።

ዩኒቨርሲቲውም ከ1 ዓመት የትሞህርት ቆይታ በኋላ ነፃ የትምህርት፣ የማደሪያና የምግብ አገልግሎቶችን አመቻችቶለታል።

ተማሪ በለጠ ቡቱና አካል ጉዳተኝነት ሳያግደው የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ካስመረቃቸው 4 ሺህ 800 ተማሪዎች ውስጥ አንዱ በመሆን በ3 ነጥብ 2 አጠቃላይ ውጤት የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል።

ወጣቱ ተመራቂ ለዚህ ምዕራፍ ባደረሰው ብርቱ የስነ-ልቦና ዝግጅት ወደፊት ለሀገሩ የላቀ አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ ስለመሆኑም ነው የተናገረው።

በመቅደስ አስፋውና ታመነ አረጋ

Exit mobile version