አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የበጎ ፈቃድ ተግባር አንዳችን ለሌላችን አለኝታነታችንን የምናሳይበት ነው ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
በክልሉ 26ኛውን ዓለም አቀፍ የሀረር ቀን በማስመልከት የተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ተከናውነዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በተገኙበት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የአቅመ ደካማ እና አረጋውያንን ዜጎች የመኖሪያ ቤት ዕድሳትና የደም ልገሳ መርሐ ግብርም ተከናውኗል፡፡
እንዲሁም በመርሐ ግብሩ በክልሉ ተወላጅ ዳያስፖራ ድጋፍ የተገኘ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚያወጣ የዊልቸር እና የክራንች ድጋፍ ለአካል ጉዳተኞች ተበርክቷል።
የዳያስፖራ አባላቱ በመድረኩ አንድ የኩላሊት እጥበት ማዕከል በመክፈት ማሽን ለማሟላትም ቃል ገብተዋል ተብሏል፡፡
በዚሁ ወቅት ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ÷ የበጎ ፈቃድ ተግባር አንዳችን ለሌላችን መከታ እና አለኝታነታችንን የምናሳይበት ነው ብለዋል፡፡
በጎነት የሰው ልጅ ቅንነት እና ደግነት ማሳያ መሆኑንም በመግለጽ በአዲስ አበባና በውጭ ሀገራት የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች የበጎ ፈቃድ ስራ ላይ ሲሳተፉ መቆየታቸውን በማስታወሰ አመስግነዋል፡፡
የዳያስፖራ አባላቱ የጀመሩትን የበጎ ፈቃድ ተግባር በቀጣይም አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ማስተላለፋቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

