አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2016 ዓ. ም የክረምት ወራት ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣቶች በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ የችግኝ ተከላ፣ የደም ልገሳ እና የአረጋውያን እንክብካቤ ስራዎችን አካሄዱ።
በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ በሚል መሪ ሀሳብ ባለፈው ሳምንት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባ ምንጭ ከተማ የተጀመረው የ2016 ዓ.ም የወጣቶች የክረምት ወራት ወሰን ተሸጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሲዳማ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ምዕራብ እና በጋምቤላ ክልሎች የችግኝ ተከላ፣ የደም ልገሳና የአካባቢ ጽዳት አካሂደዋል።
በዛሬው ዕለትም በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ ከ12ቱ ክልሎች፣ ከአዲስ አበባ ከተማ እና ድሬዳዋ አስተዳደር የተውጣጡ 80 ወጣቶች የተለያዩ የበጎ ፈቃድ ተግባራትን አከናውነዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ ወይዘሮ ሙና አህመድ በመርሐ ግብሩ ላይ እንደገለጹት÷ ዘንድሮ በሚካሄደው ሀገር አቀፍ የወጣቶች የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 34 ሚሊዮን ዜጎች ይሳተፋሉ።
በመርሐ ግብሩ ከ26 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት አገልግሎት በወጣቶቹ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን ከ49 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡
የወጣቶች የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዓላማ ወጣቶች ከሚኖሩበት አካባቢ ውጭ ያለውን ማህበረሰብ ባህል፣ እሴትና የኑሮ ዘይቤ እንዲያውቁ ማድረግ እንደሆነም ሚኒስትር ዴኤታዋ አስረድተዋል።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስተባባሪነት በበጋና በክረምት ወራት በወጣቶች በሚካሄዱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች በቢሊየን የሚቆጠር ብር ለልማት ሥራዎች መዋሉንም ጠቁመዋል፡፡
በጌታሁን ዳዲ