Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ከ7 ሚሊየን በላይ ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ ለመውሰድ መመዝገባቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እስካሁን ከ7 ሚሊየን በላይ ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ ለመውሰድ መመዝገባቸውን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የዲጅታል መታወቂያ አገልግሎት “አንድ ሰው አንድ ነው” የሚለውን መርሕ ይዞ የግለሰቦችን መረጃ በመሰብሰብ ከተለያዩ ተቋማት ጋር ቅንጅት በመፍጠር እየተካሄደ ይገኛል።

የምዝገባ ሒደቱም እስካሁን በቅንጅትና በተሳለጠ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ነው የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ያስታወቀው።

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት የተቋማት ተሳትፎ አማካሪ ኦላና አበበ÷ የዲጅታል መታወቂያ አገልግሎት ሀገራዊ ፋይዳው የላቀ መሆኑን ተናግረዋል።

የዲሞግራፊክና ባዮሜትሪክ መረጃን መዝግቦ በማዕከላዊ ቋት በመያዝ ለእያንዳንዱ ነዋሪ ልዩ ቁጥር መስጠት የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል።

በፕሮጀክቱ በቀጣይ ሶስት ዓመታት 90 ሚሊየን ዜጎችን የዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን ጠቅሰሰው፤ እስካሁን ከ7 ሚሊየን በላይ ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ ለመውሰድ መመዝገባቸውን አቶ ኦላና ለኢዜአ ገልጸዋል።

Exit mobile version