Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢዜአ እና ቲቪ ብሪክስ ኢንተርናሽናል ሚዲያ ኔትዎርክ የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ

 

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እና የቲቪ ብሪክስ ኢንተርናሽናል ሚዲያ ኔትዎርክ በጋራ መስራት የሚያስችለውን የትብብር መግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

በበይነ መረብ በተደረገው የስምምነት ፊርማ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን በመወከል አምባሳደር ረታ ዓለሙ፣ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኤቭጌኒ ቴርኪሂን እንዲሁም በሩሲያ የኢትዮጵያ ኤምባሲን በመወከል አቶ ግስላ ሻውል ተገኝተዋል።

ስምምነቱን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ እና የቲቪ ብሪክስ ኢንተርናሽናል ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጃና ቶልስተኮቫ በበይነ መረብ ፈርመውታል።

በዚሁ ጊዜ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ሕግ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ረታ ዓለሙ÷የተቋማቱ የትብብር ስምምነት ዓለም አቀፍ መረጃን ለመጋራት መሰረት የሚሆን ነው ብለዋል።

እንዲሁም ስምምነቱ መረጃን ለማሳለጥ መሰረት የሚጥል መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ÷ስምምነቱ ኢትዮጵያ አባል የሆነችበትን የብሪክስ ሚዲያ አባል ሀገራት የጋራ ጥቅሞች በሚያስጠብቅ መንገድ መረጃ ለመለዋወጥና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተደራሽ ለማድረግ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

የቲቪ ብሪክስ ኢንተርናሽናል ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጃና ቶልስተኮቫ÷ ስምምነቱ ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በጋራ ተጠቃሚነትና ትብብር ላይ የተመሰረተ ታሪካዊ ወዳጅነታቸውን ማጎልበታቸው በብሪክስ ማዕቀፍ ጎልቶ እየታየ መሆኑን የሚገልጽ ነው ብለዋል።

 

Exit mobile version