Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2017 በጀት 230 ነጥብ 39 ቢሊየን ብር ሆኖ ጸደቀ

 

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2017 በጀት 230 ነጥብ 39 ቢሊየን ብር ሆኖ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል፡፡

2ኛ ቀኑን በያዘው የአዲስ አበባ ከተማ ምክርቤት 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4 መደበኛ ጉባኤ ነው በጀቱ የጸደቀው።

የ2017 በጀት ድልድሉን ለምክር ቤት ያቀረቡት የከተማ አስተዳደሩ ፋይናንስ ቢሮ ሀላፊ አቶ አብዱልቃድር ሬድዋን÷ የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ስራዎችን ለማጠናቀቅና ለሰው ተኮር የልማት ስራዎች የካፒታል በጀቱ ከፍ ማለቱን አብራርተዋል።

በተጨማሪም በጀቱ ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ልማት፣ ለስራ ዕድል ፈጠራ፣ ለመጠጥ ውሃ፣ ለመንገድ መሰረተ ልማትና ጥራት፣ ለትራንስፖርት አገልግሎትና የከተማውን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የቴክኖሎጂ ስራ ላይ እንደሚያተኩር ተናግረዋል።

የመንግስት መደበኛ ወጪ 74 ነጥብ 55 ቢሊየን ብር እንዲሁም የካፒታል ወጪው ደግሞ 146 ነጥብ 48 ቢሊየን ብር መሆኑን ተናግረዋል።

9 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ መጠባበቂያ በጀት ሆኗል፤ የ2017 በጀት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር÷ የ68 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ወይም የ42 በመቶ ጭማሪ አለው ነው ያሉት፡፡

ለማዕከል ሴክተሮች 174 ቢሊየን ብር የተበጀተ ሲሆን÷ ለክፍለ ከተሞች ደግሞ 56 ነጥብ 16 ቢሊየን ብር መበጀቱን እና የክፍለ ከተሞች በጀትም ከከተማው አጠቃላይ በጀት 24 በመቶውን እንደሚይዝ ገልፀዋል፡፡

እንዲሁም ለመንገድ ልማት ዘርፍ 17 ቢሊየን ብር፣ ለቤቶች ልማት ዘርፍ 9 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር፣ ለአረንጓዴ ልማት ዘርፍ ደግሞ 6 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በጀት መመደቡንም አቶ አብዱልቃድር ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በበጀት ዓመቱ ከተማ አስተዳደሩ ከታክስ ገቢ 150 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር፣ ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች 43 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር፣ ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢዎች 31 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር እና ከመንገድ ፈንድ ደግሞ 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ገቢ ለማግኘትም አቅዷል።

ከውጭ ዕርዳታና ብድር ደግሞ 3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ይገኛል ተብሎ ታቅዷል።

በመሳፍንት እያዩ

Exit mobile version