Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የ1 ዓመት ከ10 ወር ህጻን ጠልፋ 500 ሺህ ብር ጠይቃ የተያዘችው ግለሰብ በጽኑ እስራት ተቀጣች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤት ሰራተኛነት ስትሰራ የ1 ዓመት ከ10 ወር ህጻንን ጠልፋ 500 ሺህ ብር ጠይቃ የተያዘችው ግለሰብ በ6 ዓመት ከ6 ወራት ጽኑ እስራት ተቀጣች።

የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ልዩ ልዩ ወንጀል ችሎት ዛሬ በዋለው ቀጠሮ አበባየሁ ሀይሌ አደሩ የተባለች ተከሳሽ ለአካለ መጠን ያልደረሰች ህጻንን መጥለፍ ወንጀል በጽኑ እስራት እንድትቀጣ ውሳኔ ሰጥቷል።

የፍትህ ሚኒስቴር ዐቃቤ ህግ ተከሳሿ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ እና ለ እንዲሁም አንቀጽ 590 ንዑስ ቁጥር 1 ለ እንዲሁም ንዑስ ቁጥር 2 (ሠ) ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፋለች በማለት በዋና ወንጀል አድራጊነት ለአካለ መጠን ያልደረሰች ህጻንን መጥለፍ ወንጀል ክስ አቅርቦባት ነበር።

በዚህ በቀረበባት ዝርዝር ክስ ላይ እንደተመላከተው፤ ተከሳሿ ነሃሴ 20 ቀን 2015 ዓ.ም ከጠዋቱ 2 ሰዓት በአዲስ አበባ ከተማ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ወረዳ 2 ዶክተሮች ማህበር እየተባለ በሚጠራ አካባቢ በቤት ሰራተኝነት ተቀጥራ ከምትሰራበት መኖሪያ ቤት የ1 ዓመት ከ10 ወር ህጻንን ጠልፋ መሸሸጓና ህጻኗን ለመመለስ የህጻኗን ወላጆች 500 ሺህ ብር ጠይቃ እንደነበርና በፀጥታ አካላት በተደረገባት ክትትል ልትያዝ እንደቻለች ተጠቅሷል።

ተከሳሿ ፍርድ ቤት ቀርባ የቀረበባትን ክስ ዝርዝር እንዲደርሳትና በንባብ ከሰማች በኋላ ተከሳሿ በክስ ዝርዝሩ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት መፈጸሟን ወይም አለመፈጸሟን ለማረጋገጥ በቀረበላት ጥያቄ መነሻ ድርጊቱን መፈጸሟን አምና ቃሏን ሰጥታለች።

ፍርድ ቤቱም የተከሳሿን ቃል እና የቀረቡ ማስረጃዎችን አገናዝቦና መርምሮ ተከሳሿን በተከሰሰችበት ድንጋጌ ስር የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባታል።

ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ በዓቃቤ ህግ የቀረበውን ማለት ተከሳሿ በአደራ የያዘቻትን ህጻን እምነቷን አጉድላ የፈጸመችው ወንጀል መሆኑን ጠቅሶ ቅጣቱ ከብዶ እንዲጣልለት የቅጣት ማክበጃ አስተያየት ያቀረበ ሲሆን÷ ተከሳሿም ቅጣቱ ቀሎ እንዲጣልላት የተለያዩ የቅጣት ማቅለያ አስተያየቶችን አቅርባለች።

ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየትን በመያዝ ተከሳሿ ጥፋተኛ በተባለችባቸው ድንጋጌ በዕርከን 24 ስር በ6 ዓመት ከ6 ወራት ጽኑ እስራት እንድትቀጣ ተወስኗል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version