Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በጎፋ ዞን በመሬት ናዳ አደጋ ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ወገኖች አፋጣኝ ምላሽ እየተሰጠ ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን በደረሰው የመሬት ናዳ አደጋ ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ወገኖች አፋጣኝ ምላሽ እየተሰጠ መሆኑን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር)በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በዞኑ በተከሰተው የመሬት ናዳ አደጋ በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል።

ሀምሌ 14 ቀን 2016 ዓ.ም በነበረው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት የመሬት ናዳው ማጋጠሙን ጠቁመዋል።

በመጀመሪያው ናዳ 4 ሰዎች መሞታቸውን እና እነዚህን ለማውጣት የሄዱ ወገኖች የሁለተኛው ናዳ ሰለባ መሆናቸውን አመላክተዋል።

ጉዳቱ ከተከሰተ ጀምሮ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።

በጉዳቱ 400 የሚሆኑ ዜጎች መፈናቀላቸውን ጠቅሰው የሚያስፈልጋቸውን ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን አንስተዋል።

አሁንም ተጨማሪ ጉዳት እንዳይፈጠር ከበርካታ ተቋማት የተውጣጡ የባለሙያዎች ቡድን ወደስፍራው መላኩን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ተፈናቃዮችን ወደ ምቹ አካባቢ የማስፈርና አስፈላጊውን ድጋፍ የማቅረብ ስራዎች ጎን ለጎን እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

 

Exit mobile version